ኦሪት ዘሌዋውያን 6

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።

2፤ ማናቸውም ሰው ኃጢአትን ቢሠራ፥ እግዚአብሔርንም ቢበድል፥ ያኖረበትን አደራ ወይም ብድር ወስዶ ባልንጀራውን ቢክድ፥ ወይም ቢቀማ፥ ወይም በባልንጀራው ላይ ግፍ ቢያደርግ፥

3፤ ወይም የጠፋውን ነገር ቢያገኝ፥ ያንንም ሸሽጎ በሐሰት ቢምል፥ ሰው ከሚያደርጋቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ ቢበድል፥

4፤ እርሱ ኃጢአትን ሠርቶ በደለኛ ቢሆን፥ በቅሚያ የወሰደውን ወይም በግፍ የተቀበለውን ወይም የተሰጠውን አደራ ወይም ጠፍቶ ያገኘውን፥

5፤ ወይም በሐሰት የማለበትን ነገር ይመልስ፤ በሙሉ ይመልስ፥ ከዚያም በላይ አምስተኛውን ክፍል ጨምሮ የበደሉን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ቀን ለባለ ገንዘቡ ይስጠው።

6፤ ስለ በደል መሥዋዕትም ለእግዚአብሔር ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ እንደ ግምጋሜህ መጠን ስለ በደል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያምጣ።

7፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ስለዚያም ስላደረገው በደል ሁሉ ይቅር ይባላል።

8፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።

9፤ አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። የሚቃጠለው የመሥዋዕቱ ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ባለው እንጨት ላይ ሌሊቱን ሁሉ እስኪጸባ ድረስ ይሆናል፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል።

10፤ ካህኑም የበፍታ ቀሚስና የበፍታ ሱሪ በሥጋው ላይ ይለብሳል፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳቱ ከበላው በኋላ አመዱን አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያፈስሰዋል።

11፤ ልብሱንም ያወልቃል፥ ሌላም ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ተሸክሞ ከሰፈሩ ንጹሕ ስፍራ ወደ ሆነ ወደ ውጭ ያወጣዋል።

12፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፥ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ እንጨት ያቃጥልበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል።

13፤ ዘወትር በመሠዊያው ላይ እሳት ይነድዳል፤ አይጠፋም።

14፤ የእህሉም ቍርባን ሕግ ይህ ነው፤ የአሮን ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በመሠዊያው ፊት ያቀርቡታል።

15፤ ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መልካሙን ዱቄት ከዘይት ጋር እፍኝ ሙሉ፥ ደግሞም በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውን ዕጣን ሁሉ ያነሣል፥ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።

16፤ ከእርሱም የተረፈውን አሮንና ልጆቹ ይበሉታል፤ ቂጣ ሆኖ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ ይበሉታል።

17፤ በእርሾ ቦክቶ አይጋገርም። እርሱን ከእሳቱ ቍርባኔ ለእነርሱ እድል ፈንታ እንዲሆን ሰጠሁ፤ እርሱም እንደ ኃጢአትና እንደ በደል መሥዋዕት ቅዱስ ቅዱሳን ነው።

18፤ ለእግዚአብሔር ከቀረበ ከእሳት ቍርባን ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ እድል ፈንታቸው እንዲሆን ከአሮን ልጆች ወንዶቹ ሁሉ ይበሉታል። የሚነካቸው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።

19፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።

20፤ በተቀቡበት ቀን የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካሙን ዱቄት እኵሌታውን በጥዋት፥ እኵሌታውንም በማታ ለዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የአሮንና የልጆቹ ቍርባን ይህ ነው።

21፤ ከዘይት ጋር በምጣድ ላይ ይደረጋል፤ ሲለወስ ታገባዋለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእህሉን ቍርባን ቈራርሰህ ታቀርበዋለህ።

22፤ ከልጆቹም በአባቱ ፋንታ የተቀባው ካህን ያቀርበዋል። ለዘላለም ሥርዓት እንዲሆን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር ይቃጠላል።

23፤ ካህኑም የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠላል፤ ከእርሱም አንዳች አይበላም።

24፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።

25፤ አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። የኃጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአቱ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል፤ እርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነው።

26፤ ለኃጢአት የሚሠዋው ካህን ይበላዋል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል።

27፤ ሥጋውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤ ማናቸው ልብስ ደም ቢረጭበት የተረጨበትን በተቀደሰ ስፍራ ታጥበዋለህ።

28፤ የሚቀቀልበትም ሸክላ ይሰበራል፤ በናስም ዕቃ ቢቀቀል ይፈገፈጋል፥ በውኃም ይለቀለቃል።

29፤ ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከእርሱ ይበላል፤ እርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነው።

30፤ ነገር ግን በመቅደሱ ውስጥ ለማስተስረያ ይሆን ዘንድ ከደሙ ወደ መገናኛው ድንኳን የሚገባው የኃጢአት መሥዋዕት ሁሉ አይበላም፤ በእሳት ይቃጠላል።