ኦሪት ዘሌዋውያን 16

1፤ በእግዚአብሔር ፊት የቀረቡና የሞቱ ሁለት የአሮን ልጆች ከሞቱ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ተናገረው፤

2፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመናው ውስጥ እታያለሁና እንዳይሞት በመጋረጃው ውስጥ በታቦቱ ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ሁልጊዜ እንዳይገባ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው።

3፤ እንዲሁ አሮን ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈን፥ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አውራ በግ ይዞ ወደ ተቀደሰ ስፍራ ይግባ።

4፤ የተቀደሰውን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፥ የበፍታውም ሱሪ በገላው ላይ ይሁን፥ የበፍታውንም መታጠቂያ ይታጠቅ፥ የበፍታውንም መጠምጠሚያ ይጠምጥም፤ እነዚህ የተቀደሱ ልብሶች ናቸው፤ ገላውንም በውኃ ታጥቦ ይልበሳቸው።

5፤ ከእስራኤልም ልጆች ማኅበር ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለት አውራ ፍየሎች፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ።

6፤ አሮንም ለእርሱ ያለውን የኃጢአቱን መሥዋዕት ወይፈን ያቀርባል፥ ለራሱም ለቤተ ሰቡም ያስተሰርያል።

7፤ ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያቆማቸዋል።

8፤ አሮንም በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጥልባቸዋል፥ አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር ሌላውንም ዕጣ ለሚለቀቅ።

9፤ አሮንም የእግዚአብሔር ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያቀርባል፥ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት ያደርገዋል።

10፤ የመለቀቅም ዕጣ የሆነበትን ፍየል ያስተሰርይበት ዘንድ፥ ለመለቀቅም ወደ ምድረ በዳ ይሰድደው ዘንድ በሕይወቱ በእግዚአብሔር ፊት ያቆመዋል።

11፤ አሮንም ስለ ራሱ ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ወይፈኑን ያቀርባል፤ ለራሱም ለቤተ ሰቡም ያስተሰርያል፤ ስለ ኃጢአቱ የእርሱን መሥዋዕት ወይፈኑን ያርዳል።

12፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናውን ይሞላል፥ ከተወቀጠውም ከጣፋጭ ዕጣን እጁን ሙሉን ይወስዳል፤ ወደ መጋረጃውም ውስጥ ያመጣዋል።

13፤ እንዳይሞትም የጢሱ ደመና በምስክሩ ላይ ያለውን መክደኛ ይሸፍን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ያደርጋል።

14፤ ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ላይ ወደ ምሥራቅ በጣቱ ይረጨዋል፤ ከደሙም በመክደኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጫል።

15፤ ስለ ሕዝቡም ኃጢአት የሚሠዋውን መሥዋዕት ፍየል ያርዳል፥ ደሙም ወደ መጋረጃው ውስጥ ያመጣዋል፤ በወይፈኑም ደም እንዳደረገ በፍየሉ ደም ያደርጋል፤ በመክደኛውም ላይና በመክደኛውም ፊት ይረጨዋል።

16፤ ከእስራኤል ልጆች ርኵስነት ከመተላለፋቸውም ከኃጢአታቸውም የተነሣ ለመቅደሱ ያስተሰርይለታል፤ እንዲሁም በርኩስነታቸው መካከል ከእነርሱ ጋር ለኖረች ለመገናኛው ድንኳን ያደርጋል።

17፤ እርሱም ለማስተስረይ ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተ ሰቡም፥ ለእስራኤል ጉባዔ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማንም አይኖርም።

18፤ በእግዚአብሔርም ፊት ወዳለው ወደ መሠዊያ ወጥቶ ያስተሰርይለታል፤ ከወይፈኑም ደም ከፍየሉም ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ቀንዶች ያስነካል።

19፤ ከደሙም በእርሱ ላይ ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል፥ ከእስራኤልም ልጆች ርኵስነት ያነጻዋል፥ ይቀድሰውማል።

20፤ መቅደሱንም፥ የመገናኛውንም ድንኳን፥ መሠዊያውንም ማስተስረይ ከፈጸመ በኋላ ሕያውን ፍየል ያቀርባል፤

21፤ አሮንም ሁለቱን እጆቹን በሕያው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፥ በላዩም የእስራኤልን ልጆች በደል ሁሉ መተላለፋቸውንም ሁሉ ኃጢአታቸውንም ሁሉ ይናዝዛል፤ በፍየሉም ራስ ላይ ያሸክመዋል፥ በተዘጋጀው ሰውም እጅ ወደ ምድረ በዳ ይሰድደዋል።

22፤ ፍየሉም ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ በረሀ ይሸከማል፤ ፍየሉንም በምድረ በዳ ውስጥ ይለቅቀዋል።

23፤ አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባል፥ ወደ መቅደሱም በገባ ጊዜ የለበሰውን የበፍታ ልብስ ያወልቃል፥ በዚያም ይተወዋል፤

24፤ በተቀደሰውም ስፍራ ገላውን በውኃ ይታጠባል፥ ሌላውንም ልብስ ለብሶ ይወጣል፤ የእርሱንም የሚቃጠል መስዋዕት፥ የሕዝቡንም የሚቃጠል መስዋዕት ያቀርባል፥ ለራሱም ለሕዝቡም ያስተሰርያል።

25፤ የኃጢያቱንም መስዋዕት ስብ በመሰዊያው ላይ ያቃጥለዋል።

26፤ ለመለቀቅ የሚሆነውን ፍየል የወሰደ ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል።

27፤ ለማስተስረያም እንዲሆን ደማቸው ወደ መቅደስ የገባውን የኃጢአቱን መስዋዕት ወይፈንና የኃጢአቱን መስዋዕት ፍየል ከሰፈሩ ወደ ውጭ ያወጡአቸዋል፤ ቁርበታቸውንም፥ ሥጋቸውንም፥ ፈርሳቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ።

28፤ ያቃጠላቸውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል።

29፤

30፤ ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ፤ በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተስረያ ይሆንላችኋልና በሰባተኛው ወር ከወሩም በአስረኛው ቀን ራሳችሁን አስጨንቋት፥ የአገር ልጅም በእናንተ መካከል የተቀመጠም እንግዳ ሥራን ሁሉ አትሥሩበት፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ።

31፤ ታላቅ ሰንበት ይሆንላችኋል፥ ራሳችሁንም ታዋርዳላችሁ፤ የዘላለም ሥርዓት ነው።

32፤ የሚቀባውም፥ በአባቱ ፋንታ ካህን ሊሆን የሚካነው ካህን ያስተስርይ፥ የተቀደሰውንም የበፍታ ልብስ ይልበስ፤

33፤ ለቅድስተ ቅዱሳኑም ያስተስርይ፤ ለመገናኛውም ድንኳን ለመሠዊያውም ያስተስርይ፤ ለካህናቱም ለጉባኤውም ሕዝብ ሁሉ ያስተስርይ።

34፤ ይህም አንድ ጊዜ በዓመት ለእስራኤል ልጆች ስለ ኃጢአታቸው ሁሉ ያስተስርይ ዘንድ የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረገ።