ኦሪት ዘሌዋውያን 18
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
3፤ እንደ ተቀመጣችሁባት እንደ ግብፅ ምድር ሥራ አትሥሩ፤ እኔም ወደ እርስዋ እንደማገባችሁ እንደ ከነዓን ምድር ሥራ አትሥሩ፤ በሥርዓታቸውም አትሂዱ።
4፤ ፍርዴን አድርጉ፥ በእርስዋም ትሄዱ ዘንድ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
5፤ የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
6፤ ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
7፤ የአባትህን ኃፍረተ ሥጋና የእናትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እናትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ።
8፤ የአባትህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህን ኃፍረተ ሥጋ ነው።
9፤ የእኅትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የእናትህ ልጅ፥ በቤት ወይም በውጭ የተወለደች ብትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ።
10፤ የወንድ ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ወይም የሴት ልጅህን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአንተ ኃፍረተ ሥጋ ነውና።
11፤ ከአባትህ የተወለደችውን የአባትህን ሚስት ልጅ ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ እህትህ ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ።
12፤ የአባትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የአባትህ ዘመድ ናት።
13፤ የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የእናትህ ዘመድ ናት።
14፤ የአባትህን ወንድም ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፥ ወደ ሚስቱም አትቅረብ፤ የአጎትህ ሚስት ናት።
15፤ የምራትህን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ኃፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ።
16፤ የወንድምህን ሚስት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድምህ ኃፍረተ ሥጋ ነው።
17፤ የሴትንና የሴት ልጅዋን ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ የወንድ ልጅዋን ሴት ልጅ ወይም የሴት ልጅዋን ሴት ልጅ ኃፍረተ ሥጋዋን ትግለጥ ዘንድ አታግባ፤ ዘመዶች ናቸው፤ ዝሙት ነው።
18፤ ሚስትህ በሕይወት ሳለች እኅትዋ ጣውንትዋ እንዳትሆን፥ ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ከእርስዋ ጋር እኅትዋን አታግባ።
19፤ እርስዋም በመርገምዋ ርኵሰት ሳለች ኃፍረተ ሥጋዋን ትገልጥ ዘንድ ወደ ሴት አትቅረብ።
20፤ እንዳትረክስባትም ከባልንጀራህ ሚስት ጋር አትተኛ።
21፤ ከዘርህም ለሞሎክ በእሳት አሳልፈህ አትስጥ፥ የአምላክህንም ስም አታርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
22፤ ከሴትም ጋር እንደምትተኛ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ጸያፍ ነገር ነውና።
23፤ እንዳትረክስባትም ከእንሰሳ ጋር አትተኛ፤ ሴት ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንድ በእንስሳ ፊት አትቁም፤ የተጠላ ነገር ነውና።
24፤ በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ።
25፤ ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፥ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች።
26፤ ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እናንተም የአገሩ ልጆች በእናንተም መካከል የሚኖሩት እንግዶች ከዚህ ርኵሰት ምንም አትሥሩ፤
27፤ ከእናንተ በፊት የነበሩ የአገሩ ልጆች ይህን ርኵሰት ሁሉ ሠርተዋልና፥ ምድሪቱም ረክሳለችና፤
28፤ ባረከሳችኋት ጊዜ ምድሪቱ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እናንተን እንዳትተፋችሁ።
29፤ ከዚህ ርኵሰት ሁሉ ማናቸውን የሚያደርግ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና።
30፤ ስለዚህ ከእናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የሠሩትን ጸያፍ የሆነውን ወግ ሁሉ እንዳትሠሩ፥ በእርሱም እንዳትረክሱ ሥርዓቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።