ኦሪት ዘሌዋውያን 17
1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2፤ ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገር። እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፥ እንዲህም አለ።
3፤ ከእስራኤል ቤት ማናቸውም ሰው በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ቢያርድ፥ በሰፈሩ ውስጥ ወይም ከሰፈሩ ውጭ ቢያርደው፥
4፤ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር ቍርባን ያቀርብ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ደሙ በዚያ ሰው ላይ ይቈጠርበታል፤ ደም አፍስሶአል፤ ያም ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
5፤ ስለዚህ የእስራኤል ልጆች በሜዳ የሚያርዱትን መሥዋዕታቸውን ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያመጡታል፤ ወደ ካህኑም አምጥተው ለእግዚአብሔር ለደኅንነት መሥዋዕት ይሠዉታል።
6፤ ካህኑም በመገኛኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ደሙን ይረጨዋል፥ ስቡንም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ያቃጥለዋል።
7፤ መሥዋዕታቸውንም ደግሞ ተከትለው ላመነዘሩባቸው ለሰይጣናት አይሠዉ። ይህ ለእነርሱ ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ሥርዓት ይሁን።
8፤ ለእነርሱም እንዲህ በላቸው። ከእስራኤል ቤት በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት ቢያቀርብ፥
9፤ ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
10፤ ከእስራኤልም ልጆች ወይም በመካከላቸው ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው ደም ቢበላ፥ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፥ ያንንም ሰው ከሕዝቡ ለይቼ አጠፋዋለሁ።
11፤ የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት።
12፤ ስለዚህ የእስራኤልን ልጆች። ከእናንተ ማንም ደምን አይበላም፥ በመካከላችሁም ከሚኖሩ እንግዶች ማንም ደምን አይበላም አልሁ።
13፤ ከእስራኤልም ልጆች በመካከላቸውም ከሚኖሩ እንግዶች ማናቸውም ሰው የሚበላ እንስሳ ወይም ወፍ እያደነ ቢይዝ፥ ደሙን ያፈስሳል በአፈርም ይከድነዋል።
14፤ የሥጋ ሁሉ ሕይወትና ደሙ አንድ ነውና ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች። የሥጋ ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የሥጋውን ሁሉ ደም አትብሉ፤ የሚበላውም ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ አልኋቸው።
15፤ የሞተውን ወይም አውሬ የሰበረውን የሚበላ ሰው ሁሉ፥ የአገር ልጅ ወይም እንግዳ ቢሆን፥ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።
16፤ ልብሱንና ገላውን ባያጥብ ግን ኃጢአቱን ይሸከማል።