ኦሪት ዘሌዋውያን 10
1፤ የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ።
2፤ እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ።
3፤ ሙሴም አሮንን። እግዚአብሔር። ወደ እኔ በሚቀርቡ እቀድሳለሁ፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ ብሎ የተናገረው ይህ ነው አለው፤ አሮንም ዝም አለ
4፤ ሙሴም የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ። ቅረቡ፥ ወንድሞቻችሁንም ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዱአቸው አላቸው።
5፤ እነርሱም ቀርበው አነሡአቸው፥ ሙሴም እንዳለ በቀሚሳቸው ከሰፈር ወደ ውጭ ወሰዱአቸው።
6፤ ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን። እንዳትሞቱ በማኅበሩም ሁሉ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ራሳችሁን አትንጩ፥ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ እግዚአብሔር ስላቃጠለው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ።
7፤ የእግዚአብሔር የቅብዓት ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትወጡም አላቸው። እንደ ሙሴ ቃልም አደረጉ።
8፤ እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
9፤ እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤
10፤ በተቀደሰውና ባልተቀደሰው፥ በርኩሱና በንጹሑም መካከል ትለያላችሁ፤
11፤ እግዚአብሔርም በሙሴ ቃል የነገራቸውን ሥርዓት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ታስተምራላችሁ።
12፤ ሙሴም አሮንን፥ የተረፉለትንም ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን አላቸው። ቅዱስ ቅዱሳን ነውና ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቁርባን የቀረውን የእህሉን ቁርባን ውሰዱ፥ ቂጣም አድርጋችሁ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት እግዚአብሔርም እንዲህ አዞኛል፥
13፤ ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቁርባን ለአንተም ለልጆችህም የተሰጠ ሥርዓት ነውና በቅዱስ ስፍራ ትበሉታላችሁ።
14፤ እነዚህም ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕቶች ለአንተና ለልጆችህ ሥርዓት እንዲሆኑ ስለ ተሰጡ፥ የሚወዘወዘውን ፍርምባ፥ የሚነሣውንም ወርች አንተ፥ ከአንተ ጋርም ልጆችህ፥ ሴቶች ልጆችህም በንጹሕ ስፍራ ትበላላችሁ።
15፤ የሚነሣውን ወርች የሚወዘወዘውንም ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን እንዲወዘውዙ የእሳት ቁርባን ከሆነው ስብ ጋር ያመጣሉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለአንተ ከአንተ ጋርም ለልጆችህ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል።
16፤ ሙሴም የኃጢያቱን መሥዋዕት ፍየል እጅግ ፈለገው፥ እነሆም ተቃጥሎ ነበር፤ ሙሴም የቀሩትን የአሮንን ልጆች አልአዛርንና ኢታምርን ተቈጥቶ።
17፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነውና፥ የሕዝቡንም ኃጢያት እንድትሸከሙ፥ በእግዚአብሔርም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ለእናንተ ሰጥቶታልና ስለ ምን የኃጢያትን መሥዋዕት በቅዱሱ ስፍራ አልበላችሁም?
18፤ እነሆ ደሙን ወደ መቅደሱ ውስጥ አላገባችሁትም፤ እኔ እንዳዘዝሁ በቅዱሱ ስፍራ ውስጥ ትበሉት ዘንድ ይገባችሁ ነበር አላቸው።
19፤ አሮንም ሙሴን። እነሆ ዛሬ የኃጢያታቸውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፤ ይህም ሁሉ ደረሰብኝ፤ ዛሬስ የኃጢያት መሥዋዕት በበላሁ ኖሮ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ኖሮአልን? አለው።
20፤ ሙሴም ሰማ በፊቱም መልካም ሆነ።