ትንቢተ ኢሳይያስ 30
1፤ ለዓመፀኞች ልጆች ወዮላቸው! ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ ዘንድ ያልሆነን ምክር ይመክራሉ፥ ኃጢአትንም በኃጢአት ላይ ይጨምሩ ዘንድ ከመንፈሴ ዘንድ ያልሆነውን ቃል ኪዳን ያደርጋሉ።
2፤ ከአፌም ነገርን ሳይጠይቁ በፈርዖን ኃይል ይጸኑ ዘንድ በግብጽም ጥላ ይታመኑ ዘንድ ወደ ግብጽ እንዲወርዱ ይሄዳሉ።
3፤ ስለዚህ የፈርዖን ኃይል እፍረት በግብጽም ጥላ መታመን ስድብ ይሆንባችኋል።
4፤ አለቆች ምንም በጣኔዎስ ቢሆኑ፥ መልክተኞችም ምንም ወደ ሓኔስ ቢደርሱ፥
5፤ ሁላቸው ይጠቅሙአቸው ዘንድ ስለማይችሉ፥ እፍረትና ስድብ እንጂ ረድኤትና ረብ ስለማይሆኑ ሕዝብ ያፍራሉ።
6፤ በደቡብ ስላሉ እንስሶች የተነገረ ሸክም። ተባትና እንስት አንበሳ እፉኝትም ነዘር እባብም በሚወጡባት በመከራና በጭንቀት ምድር በኩል ብልጥግናቸውን በአህዮች ጫንቃ ላይ መዛግብቶቻቸውንም በግመሎች ሻኛ ላይ እየጫኑ ወደማይጠቅሙአቸው ሕዝብ ይሄዳሉ።
7፤ የግብጽ እርዳታ ከንቱና ምናምን ነው፤ ስለዚህ ስሙን። በቤት የሚቀመጥ ረዓብ ብዬ ጠርቼዋለሁ።
8፤ አሁንም ሂድ፥ ለሚመጣውም ዘመን ለዘላለም እንዲሆን በሰሌዳ ላይ በመጽሐፍም ውስጥ ጻፍላቸው።
9፤ ዓመፀኛ ወገንና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመስማት የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና፤
10፤ ባለ ራእዮችን። አትመልከቱ ይላሉ፥ ነቢያትንም። ጣፋጩንና አታላዩን ነገር እንጂ ቅኑን ነገር አትንገሩን ከመንገድ ፈቀቅ በሉ፥
11፤ ከጐዳናውም ዘወር በሉ፥ የእስራኤልንም ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ ይሉአቸዋል።
12፤ ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል። ይህችን ቃል አቃልላችኋልና፥ በግፍና በጠማምነት ታምናችኋልና፥ በእርሱም ተደግፋችኋልና
13፤ ስለዚህ ይህ በደል አዘብዝቦ ለመፍረስ እንደ ቀረበ፥ አፈራረሱም ፈጥኖ ድንገት እንደሚመጣ እንደ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል።
14፤ የሸክለኛ ማድጋ እንደሚሰበር ይሰብረዋል፥ ሳይራራም ያደቅቀዋል፤ ከስባሪውም እሳት ከማንደጃ የሚወስዱበት ወይም ውኃ ከጕድጓድ የሚቀዱበት ገል አይገኝም።
15፤ የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ እናንተም እንቢ አላችሁ፥
16፤ ነገር ግን። በፈረስ ላይ ትቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም አላችሁ፥ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ደግሞም። በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን አላችሁ፥ ስለዚህም የሚያሳድዱአችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ።
17፤ ከአንድ ሰው ዛቻ የተነሣ ሺህ ሰዎች ይሸሻሉ፤ እናንተም በተራራ ራስ ላይ እንዳለ ምሰሶ፥ በኮረብታም ላይ እንዳለ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፥ ከአምስት ሰዎች ዛቻ የተነሣ ትሸሻላችሁ።
18፤ እግዚአብሔርም የፍርድ አምላክ ነውና ስለዚህ እግዚአብሔር ይራራላችሁ ዘንድ ይታገሣል፥ ይምራችሁም ዘንድ ከፍ ከፍ ይላል፤ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።
19፤ በኢየሩሳሌም ውስጥ በጽዮን የምትኖሩ ሕዝብ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅስም፤ በጩኸትም ድምፅ ይራራልሃል፥ በሰማህም ጊዜ ይመልስልሃል።
20፤ ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን ውኃ ቢሰጥህም አስተማሪህ እንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፤ ዓይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፥
21፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ። መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ።
22፤ በብርም የተለበጡትን የተቀረጹትን ምስሎችህን በወርቅም የተለበጡትን ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችህን ታረክሳለህ፤ እንደ ርኩስም ነገር ትጥላቸዋለህ። ወግዱ ትላቸውማለህ።
23፤ በምድርም ለተዘራው ዘርህ ዝናብ ይሰጣል፥ ከምድርም ፍሬ የሚወጣ እንጀራ ወፍራምና ብዙ ይሆናል። በዚያም ቀን ከብቶችህ በሰፊ መስክ ይሰማራሉ፤
24፤ መሬትንም የሚያርሱ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በወንፊት የነጻውን ጨው ጨው የሚለውን ገፈራ ይበላሉ።
25፤ በታላቅም እልቂት ቀን ግንቦች በወደቁ ጊዜ በረጅሙ ተራራ ሁሉ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ ወንዞችና የውኃ ፈሳሾች ይሆናሉ።
26፤ እግዚአብሔርም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፥ መቅሰፍቱ የቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት፥ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን፥ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይሆናል።
27፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ስም ከሚነድድ ቍጣ ከሚትጐለጐልም ጢስ ጋር ከሩቅ ይመጣል፤ ከንፈሮቹም ቍጣን የሞሉ ናቸው፥ ምላሱም እንደምትበላ እሳት ናት፤
28፤ እስትንፋሱም አሕዛብን በአጥፊ ወንፊት ሊነፋቸው እንደሚያጥለቀልቅ እስከ አንገትም እንደሚደርስ ወንዝ ነው፥ በሕዝብም መንጋጋ የሚያስት ልጓም ይሆናል።
29፤ ዝማሬ በተቀደሰች የዐውደ ዓመት ሌሊት እንደሚሆን ዝማሬ ይሆንላችኋል፤ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ እስራኤል አምባ ይመጣ ዘንድ እንቢልታ ይዞ እንደሚሄድ ሰው የልብ ደስታ ይሆንላችኋል።
30፤ እግዚአብሔርም ክቡር ድምፁን ያሰማል፥ የክንዱንም መውረድ በሚነድድ ቍጣውና በምትበላ እሳት ነበልባል በዐውሎ ነፋስም በወጨፎም በበረዶ ጠጠርም ይገልጣል።
31፤ አሦርም በበትር ከመታው ከእግዚአብሔር ድምፅ የተነሣ ይደነግጣል።
32፤ እግዚአብሔር በላዩ በሚያወርድበት የታዘዘበቱ የበትር ድብደባ ሁሉ በከበሮና በመሰንቆ ይሆናል፤ በጦርነትም ክንዱን አንሥቶ ይዋጋቸዋል።
33፤ ከቀድሞም ጀምሮ የማቃጠያ ስፍራ ተዘጋጅታለች፥ ለንጉሥም ተበጅታለች፤ ጥልቅና ሰፊም አድርጎአታል፤ እሳትና ብዙ ማገዶ ተከምሮአል፤ የእግዚአብሔርም እስትንፋስ እንደ ዲን ፈሳሽ ያቃጥለዋል።