ትንቢተ ኢሳይያስ 26
1፤ በዚያም ቀን ይህ ቅኔ በይሁዳ ምድር ይዘመራል። የጸናች ከተማ አለችን፤ ለቅጥርና ለምሽግ መድኃኒትን ያኖርባታል።
2፤ እውነትን የሚጠብቅ ጻድቅ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ።
3፤ በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።
4፤ ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነውና ለዘላለም በእግዚአብሔር ታመኑ።
5፤ በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ያደርጋል፤ ከፍ ያለችውን ከተማ ያዋርዳል፥ እስከ መሬትም ድረስ ያዋርዳታል፥ እስከ አፈርም ድረስ ይጥላታል።
6፤ እግር፥ የድሀ እግርም የችግረኛም አረጋገጥ፥ ትረግጣታለች።
7፤ የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፤ አንተ ቅን የሆንህ የጻድቃንን መንገድ ታቃናለህ።
8፤ አቤቱ፥ በፍርድህ መንገድ ተስፋ አድርገንሃል፥ ስምህም መታሰቢያህም የነፍሳችን ምኞት ነው።
9፤ ፍርድህን በምድር ባደረግህ ጊዜ በዓለም የሚኖሩት ጽድቅን ይማራሉና ነፍሴ በሌሊት ትናፍቅሃለች፥ መንፈሴም በውስጤ ወደ አንተ ትገሠግሣለች።
10፤ ለኃጢአተኛ ሞገስ ቢደረግለት ጽድቅን አይማርም፤ በቅኖች ምድር ክፉን ነገር ያደርጋል፥ የእግዚአብሔርንም ግርማ አያይም።
11፤ አቤቱ፥ እጅህ ከፍ ከፍ አለች አላዩምም፤ ነገር ግን በሕዝብህ ላይ ያለህን ቅንዓት አይተው ያፍራሉ፤ እሳትም ጠላቶችህን ትበላለች።
12፤ አቤቱ፥ ሥራችንን ሁሉ ሠርተህልናልና ሰላምን ትሰጠናለህ።
13፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ ከአንተ በቀር ሌሎች ጌቶች ገዝተውናል፤ ነገር ግን በአንተ ብቻ ስምህን እናስባለን።
14፤ እነርሱ ሞተዋል፥ በሕይወት አይኖሩም፤ ጠፍተዋል፥ አይነሡም፤ ስለዚህ አንተ ጐብኝተሃቸዋል አጥፍተሃቸውማል፥ መታሰቢያቸውንም ሁሉ ምንምን አድርገሃል።
15፤ ሕዝብን አበዛህ፥ አቤቱ፥ ሕዝብን አበዛህ፤ አንተም ተከበርህ፥ የአገሪቱንም ዳርቻ ሁሉ አሰፋህ።
16፤ አቤቱ፥ በመከራ ጊዜ ፈለጉህ፥ በገሰጽሃቸውም ጊዜ ልመናቸውን ወደ አንተ አፈሰሱ።
17፤ የፀነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና በምጥ እንደምትጮኽ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ በፊትህ ሆነናል።
18፤ እኛ ፀንሰናል ምጥም ይዞናል፥ ነፋስንም እንደምንወልድ ሆነናል፤ በምድርም ደኅንነት አላደረግነም፤ በዓለምም የሚኖሩ ይወድቃሉ።
19፤ ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፥ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፥ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም።
20፤ ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።
21፤ በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቍጣውን ያመጣባቸው ዘንድ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፤ ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፥ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።