0:00

ትንቢተ ኢሳይያስ 22

1፤ ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ሸክም። እናንተ ሁላችሁ ወደ ሰገነት መውጣታቸሁ ምን ሆናችኋል?

2፤ ጩኸትና ፍጅት የተሞላብሽ ከተማ፥ ደስታ ያለሽ ከተማ ሆይ፥ በአንቺ ውስጥ የተገደሉት በሰይፍ የተገደሉ አይደሉም፥ በሰልፍም የሞቱ አይደሉም።

3፤ አለቆችሽ ሁሉ በአንድነት ሸሹ፥ ያለ ቀስትም ተማረኩ፤ ከሩቅ ሸሽተው ከአንቺ ዘንድ የተገኙት ሁሉ በአንድነት ታሰሩ።

4፤ ስለዚህ። ፊታችሁን ከእኔ ዘንድ አርቁ፤ መራራ ልቅሶ አለቅሳለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት ታጽናኑኝ ዘንድ አትድከሙ አልሁ።

5፤ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የድንጋጤና የመረገጥ የድብልቅልቅም ቀን፥ የቅጥርም መፍረስ ወደ ተራራም መጮኽ በራእይ ሸለቆ ውስጥ ሆኖአል።

6፤ ኤላምም ከሰረገለኞችና ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ አፎቱን ተሸከመ፥ ቂርም ጋሻውን ገለጠ።

7፤ መልካሞቹንም ሸለቆችሽን ሰረገሎች ሞሉባቸው፥ ፈረሰኞችም መቆሚያቸውን በበር ላይ አደረጉ።

8፤ የይሁዳንም መጋረጃ ገለጠ፤ በዚያም ቀን በዱር ቤት የነበረውን የጦር ዕቃ ተመለከትህ፥

9፤ የዳዊትም ከተማ ፍራሾች እንደ በዙ አይታችኋል፥ የታችኛውንም ኵሬ ውኃ አከማችታችኋል፥

10፤ የኢየሩሳሌምን ቤቶች ቈጠራችሁ ቅጥሩንም ለማጥናት ቤቶችን አፈረሳችሁ።

11፤ በአሮጌው ኵሬ ላለው ውኃ በሁለቱ ቅጥር መካከል መከማቻ ሠራችሁ፤ ይህን ያደረገውን ግን አልተመለከታችሁም፥ ቀድሞ የሠራውንም አላያችሁም።

12፤ በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ልቅሶና ወደ ዋይታ ራስን ወደ መንጨትና ማቅንም ወደ መልበስ ጠራ።

13፤ እነሆም፥ ሐሜትና ደስታ በሬውንና በጉንም ማረድ ሥጋንም መብላት የወይን ጠጅንም መጠጣት ሆነዋል፤ እናንተ። ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ ብላችኋል።

14፤ ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ። እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

15፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በቤቱ ውስጥ ወደ ተሾመው ወደዚህ አዛዥ ወደ ሳምናስ ሂድ እንዲህም በለው።

16፤ መቃብር በዚህ ያስወቀርህ ከፍ ባለው ስፍራ መቃብር ያሰራህ በድንጋይም ውስጥ ለራስህ መኖርያ ያሳነጽህ በዚህ ምን አለህ? በዚህስ በአንተ ዘንድ ማን አለ?

17፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይል ወርውሮ ይጥልሃል፥ አጠንክሮም ይጨብጥሃል።

18፤ ጠቅልሎም ያንከባልልሃል ወደ ሰፊይቱም ምድር እንደ ኳስ ይጥልሃል፤ አንተ የጌታህ ቤት እፍረት! በዚያ ትሞታለህ በዚያም የክብርህ ሰረገላዎች ይሆናሉ።

19፤ ከአዛዥነት ሥራህ አሳድድሃለሁ፥ ከሹመትህም ትሻራለህ።

20፤ በዚያም ቀን ባሪያዬን የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን እጠራለሁ፥

21፤ መጐናጸፊያህንም አለብሰዋለሁ፥ በመታጠቂያህም አስታጥቀዋለሁ፥ ሹመትህንም በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለይሁዳም ቤት አባት ይሆናል።

22፤ የዳዊትንም ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ይከፍታል የሚዘጋም የለም እርሱም ይዘጋል የሚከፍትም የለም።

23፤ በታመነም ስፍራ እንደ ችንካር እተክለዋለሁ፥ ለአባቱም ቤት የክብር ዙፋን ይሆናል።

24፤ የአባቱንም ቤት ክብር ሁሉ ልጆቹንም የልጅ ልጆቹንም፥ ከጽዋ ዕቃ ጀምሮ እስከ ማድጋ ዕቃ ድረስ፥ ታናናሹን ዕቃ ሁሉ ይሰቅሉበታል።

25፤ በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ በታመነው ስፍራ የተከለው ችንካር ይወልቃል ተሰብሮም ይወድቃል፥ በእርሱም ላይ የተሰቀለው ሸክም ይጠፋል እግዚአብሔር ተናግሮአልና።