ትንቢተ ኢሳይያስ 21
1፤ በባሕር አጠገብ ስላለው ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ሸክም። ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እንደሚወጣ፥ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር ከምድረ በዳ ይወጣል።
2፤ ከባድ ራእይ ተነገረኝ፤ ወንጀለኛው ይወነጅላል አጥፊውም ያጠፋል። ኤላም ሆይ፥ ውጪ፤ ሜዶን ሆይ፥ ክበቢ፤ ትካዜውን ሁሉ አስቀርቻለሁ።
3፤ ስለዚህ ወገቤ ሕመም ተሞላ፤ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ያዘኝ፤ ከሕመሜ የተነሣ አልሰማም፥ ከድንጋጤም የተነሣ አላይም።
4፤ ልቤ ተንበደበደ፥ ድንጋጤ አስፈራኝ፥ ተስፋ ያደረግሁትም ድንግዝግዝታ መንቀጥቀጥ ሆነብኝ።
5፤ ማዕዱን ያዘጋጃሉ፥ ምንጣፉንም ይዘረጋሉ፥ ይበሉማል፥ ይጠጡማል፤ እናንተ መሳፍንት ሆይ፥ ተነሡ፥ ጋሻውን አዘጋጁ።
6፤ ጌታ እንዲህ ብሎኛልና። ሂድ ጉበኛም አቁም፥ የሚያየውንም ይናገር።
7፤ በከብት የሚቀመጡትን፥ ሁለት ሁለት እየሆኑ የሚሄዱት ፈረሰኞች፥ በአህዮች የሚቀመጡትንና በግመሎች የሚቀመጡትን ባየ ጊዜ በጽኑ ትጋት አስተውሎ ተግቶም ያድምጥ።
8፤ ያየውም። ጌታ ሆይ፥ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፥ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ፥
9፤ እነሆም፥ በፈረሶች የሚቀመጡ፥ ሁለት ሁለት ሁነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ ብሎ ጮኸ፤ እርሱም መልሶ። ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፥ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ።
10፤ እናንተ በአውድማዬ ላይ የተወቃችሁ የአውድማዬ ልጆች ሆይ፥ ከእስራኤል አምላክ ከሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሰማሁትን ነገርኋችሁ።
11፤ ስለ ኤዶምያስ የተነገረ ሸክም። አንዱ ከሴይር። ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ብሎ ጠራኝ።
12፤ ጕበኛውም። ይነጋል ድግሞም ይመሻል፤ ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ፤ ተመልሳችሁም ኑ አለ።
13፤ ስለ ዓረብ የተነገረ ሸክም። የድዳናውያን ነጋዴዎች ሆይ፥ በዓረብ ዱር ውስጥ ታድራላችሁ።
14፤ በቴማን የምትኖሩ ሆይ፥ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ እንጀራ ይዛችሁ የሸሹትን ሰዎች ተቀበሉአቸው።
15፤ ከሰይፍ፥ ከተመዘዘው ሰይፍ፥ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና።
16፤ ጌታ እንዲህ ብሎኛልና። እንደ ምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ክብር ሁሉ ይጠፋል፤
17፤ ከቀስተኞች ቍጥር የቀሩት፥ የቄዳር ልጆች ኃያላን፥ ያንሳሉ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።