መጽሐፈ ኢዮብ። 31

1፤ ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲህስ ቈንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?

2፤ የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ከላይ፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ርስት ከአርያም ምንድር ነው?

3፤ መዓትስ ለኃጢአተኛ፥ መለየትስ ለሚበድሉ አይደለምችን?

4፤ መንገዴን አያይምን? እርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?

5፤

6፤ በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥ እግዚአብሔርም ቅንነቴን ይወቅ። በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነ እግሬም ለሽንገላ ቸኵላ እንደ ሆነ፥

7፤ እርምጃዬ ከመንገድ ፈቀቅ ብሎ፥ ልቤም ዓይኔን ተከትሎ፥ ነውርም ከእጄ ጋር ተጣብቆ እንደ ሆነ፥

8፤ እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፤ የሚበቅለውም ሁሉ ይነቀል።

9፤ ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጐምጅቶ እንደ ሆነ፥ በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደ ሆነ፥

10፤ ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፥ ሌሎችም በእርስዋ ላይ ይጐንበሱ።

11፤ ይህ ክፉ አበሳ፥ ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና፤

12፤ ይህ እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት፥ ቡቃያዬንም ሁሉ የሚነቅል ነውና።

13፤ ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፥ ሙግታቸውን ንቄ እንደ ሆነ፥

14፤ እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ? በጐበኘኝ ጊዜ ምን እመልስለታለሁ?

15፤ እኔን በማኅፀን የፈጠረ እርሱንስ የፈጠረው አይደለምን? በማኅፀንስ ውስጥ የሠራን አንድ አይደለንምን?

16፤ ድሀውን ከልመናው ከልክዬ፥ የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደ ሆነ፥

17፤ እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥ ድሀ አደጉም ደግሞ ከእርሱ ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፤

18፤ እርሱን ግን ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባቱ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥ እርስዋንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፤

19፤ ራቁቱን የሆነው ሰው ሲጠፋ፥ ወይም ድሀ ያለ ልብስ ሲሆን አይቼ እንደ ሆነ፥

20፤ ጐንና ጐኑ ያልባረከችኝ፥ በበጎቼም ጠጕር ያልሞቀ እንደ ሆነ፤

21፤ በበሩ ረዳት ስላየሁ፥ በድሀ አደጉ ላይ እጄን አንሥቼ እንደ ሆነ፥

22፤ ትከሻዬ ከመሠረትዋ ትውደቅ፥ ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር።

23፤ የእግዚአብሔር መዓት አስደንግጦኛልና፤ በክብሩም ፊት ምንም ለማድረግ አልቻልሁም።

24፤ ወርቅን ተስፋ አድርጌ፥ ጥሩውንም ወርቅ። በአንተ እታመናለሁ ብዬ እንደ ሆነ፤

25፤ ሀብቴ ስለ በዛ፥ እጄም ብዙ ስላገኘች ደስ ብሎኝ እንደ ሆነ፤

26፤ ፀሐይ ሲበራ ጨረቃ በክብር ስትሄድ አይቼ፥

27፤ ልቤ በስውር ተታልሎ፥ አፌም እጄን ስሞ እንደ ሆነ፤

28፤ ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርና ይህ ደግሞ ፈራጆች የሚቀጡበት በደል በሆነ ነበር።

29፤ በሚጠላኝ መጥፋት ደስ ብሎኝ ክፉ ነገርም ባገኘው ጊዜ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፤

30፤ ነገር ግን በመርገም ነፍሱን በመሻት አንደበቴን ኃጢአት ይሠራ ዘንድ አልሰጠሁም፤

31፤ በድንኳኔ የሚኖሩ ሰዎች። በከብቱ ሥጋ ያልጠገበ ማን ይገኛል? ብለው እንደ ሆነ፤

32፤ መጻተኛው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፥ ደጄንም ለመንገደኛ እከፍት ነበር፤

33፤ በደሌንም በብብቴ በመሸሸግ ኃጢአቴን እንደ ሰው ሰውሬ እንደ ሆነ፤

34፤ ከሕዝብ ብዛት ፈርቼ፥ የዘመዶቼም ንቀት አስደንግጦኝ፥ ዝም ብዬ ከደጅ ያልወጣሁ እንደ ሆነ፤

35፤ የሚያዳምጠኝ ምነው በኖረልኝ! እነሆ የእጄ ምልክት ሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ፤ ከባላጋራዬ የተጻፈው የክስ ጽሑፍ ምነው በተገኘልኝ!

36፤ በትከሻዬ ላይ እሸከመው፥ አክሊልም አድርጌ በራሴ አስረው ነበር፤

37፤ የእርምጃዬን ቍጥር አስታውቀው፥ እንደ አለቃም ሆኜ አቀርብለት ነበር።

38፤ እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ እንደ ሆነ፥ ትልሞችዋም በአንድ ላይ አልቅሰው እንደ ሆነ፤

39፤ ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፥ የባለቤቶችንም ነፍስ አሳዝኜ እንደ ሆነ፥

40፤ በስንዴ ፋንታ አሜከላ፥ በገብስም ፋንታ ኵርንችት ይውጣብኝ። የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።