መጽሐፈ ኢዮብ። 14
1፤ ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፥ መከራም ይሞላዋል።
2፤ እንደ አበባ ይወጣል፥ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላም ይሸሻል፥ እርሱም አይጸናም።
3፤ እንደዚህስ ባለ ሰው ላይ ዓይኖችህን ትከፍታለህን? ከአንተስ ጋር እኔን ወደ ፍርድ ታገባለህን?
4፤ ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም።
5፤ የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥ የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት።
6፤ እንደ ምንደኛ ዕድሜው እስኪፈጸም ድረስ ያርፍ ዘንድ ከእርሱ ጥቂት ዘወር በል።
7፤ ዛፍ ቢቈረጥ ደግሞ ያቈጠቍጥ ዘንድ፥ ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው።
8፤ ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ ግንዱም በመሬት ውስጥ ቢሞት፥
9፤ ከውኃ ሽታ የተነሣ ያቈጠቍጣል፤ እንደ አትክልት ቅርንጫፍ ያወጣል።
10፤ ሰው ግን ይሞትና ይጋደማል፤ ሰውም ነፍሱን ይሰጣል፥ እርሱስ ወዴት አለ?
11፤ ውኃ ከባሕር ውስጥ ያልቃል፤ ወንዙም ያንሳል ይደርቅማል።
12፤ ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም።
13፤ በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቍጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ!
14፤ በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፥ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር።
15፤ በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።
16፤ አሁን ግን እርምጃዬን ቈጥረኸዋል፤ ኃጢአቴንም ትጠባበቃለህ።
17፤ መተላልፌ በከረጢት ውስጥ ታትሞአል፥ ኃጢአቴንም ለብጠህበታል።
18፤ ተራራ ሲወድቅ ይጠፋል፥ ዓለቱም ከስፍራው ይፈልሳል፤
19፤ ውኆች ድንጋዮቹን ይፍቃሉ፤ ፈሳሾቹም የምድሩን አፈር ይወስዳሉ፤ እንዲሁ የሰውን ተስፋ ታጠፋዋለህ።
20፤ ለዘላለም ታሸንፈዋለህ፥ እርሱም ያልፋል፤ ፊቱን ትለውጣለህ፥ እርሱንም ትሰድደዋለህ።
21፤ ልጆቹ ቢከብሩ አያውቅም፤ ቢዋረዱም አያይም።
22፤ ነገር ግን የገዛ ሥጋው ሕመም ብቻ ይሰማዋል፥ ለራሱም ብቻ ያለቅሳል። ች