መጽሐፈ ኢዮብ። 15

1፤ ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ።

2፤ በውኑ ጠቢብ ሰው እንደ ንፋስ በሆነ እውቀት ይመልሳልን? በሆዱስ የምሥራቅን ነፋስ ይሞላልን?

3፤ ከማይረባ ነገር፥ ወይስ ከማይጠቅም ንግግር ጋር ይዋቀሳልን?

4፤ አንተም እግዚአብሔርን መፍራት ታፈርሳለህ፤ በእግዚአብሔር ፊት አምልኮን ታስቀራለህ።

5፤ በደልህ አፍህን ያስተምረዋል፥ የተንኰለኞችንም አንደበት ትመርጣለህ።

6፤ የሚፈርድብህ አፍህ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። ከንፈሮችህም ይመሰክሩብሃል።

7፤ በውኑ መጀመሪያ የተወለድህ ሰው አንተ ነህን? ወይስ ከተራሮች በፊት ተፀነስህን?

8፤ የእግዚአብሔርንስ ምሥጢር ሰምተሃልን? ወይስ ጥበብን ለብቻህ አድርገሃልን?

9፤ እኛ የማናውቀውን አንተ የምታወቀው ምንድር ነው? ከእኛ ዘንድስ የሌለው የምታስተውለው ምንድር ነው?

10፤ በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ ሽበትም ያላቸው ሽማግሌዎችም ከእኛ ጋር አሉ።

11፤ በውኑ የእግዚአብሔር ማጽናናት፥ በየውሃትም የተነገረህ ቃል ጥቂት ነውን?

12፤ ልብህስ ለምን ይወስድሃል? ዓይኖችህስ ለምን ይገለምጣሉ?

13፤ በእግዚአብሔር ላይ መንፈስህን እስከ ማንሣት ደርሰህ፤ ይህንም ቃል ከአፍህ እስከ ማውጣት ደርሰህ።

14፤ ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ምንድር ነው?

15፤ እነሆ፥ በቅዱሳኑ ስንኳ አይታመንም፤ ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።

16፤ ይልቁንስ አስጸያፊና የረከሰ፥ ኃጢአትንም እንደ ውኃ የሚጠጣ ሰው ምንኛ ያንስ?

17፤

18፤ ምድሪቱ ለብቻቸው ተሰጥታ የነበረች፥

19፤ በመካከላቸውም እንግዳ ያልገባባቸው ጠቢባን። ከአባቶቻቸው ተቀብለው የተናገሩትን ያልሸሸጉትንም፥ እገልጥልሃለሁ፥ ስማኝ፤ ያየሁትንም እነግርሃለሁ።

20፤ ክፉ ሰው ዕድሜውን ሙሉ፥ ከግፈኛ በተመደቡለት በዓመታት ሁሉ በሕመም ይጣጣራል።

21፤ የሚያስደነግጥ ድምፅ በጆሮው ነው፤ በደኅንነቱም ሳለ ቀማኛ ይመጣበታል።

22፤ ከጨለማ ተመልሶ እንዲወጣ አያምንም፥ ሰይፍም ይሸምቅበታል።

23፤ ተቅበዝብዞም። ወዴት አለ? እያለ እንጀራ ይለምናል፤ የጨለማ ቀን እንደ ቀረበበት ያውቃል።

24፤ መከራና ጭንቀት ያስፈራሩታል፤ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ንጉሥ ያሸንፉታል፤

25፤ እጁን በእግዚአብሔር ላይ ዘርግቶአልና፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ ላይ ደፍሮአልና፥

26፤ በደንዳና አንገቱና በወፍራሙ በጋሻው ጕብጕብ እየሠገገ ይመጣበታልና፥

27፤ በስብም ፊቱን ከድኖአልና፥ ስቡንም በወገቡ ላይ አድርጓልና፥

28፤ በተፈቱም ከተሞች ውስጥ፥ ሰውም በሌለባቸው፥ ክምር ለመሆን በተመደቡ ቤቶች ውስጥ ተቀምጦአልና

29፤ ባለጠጋ አይሆንም፥ ሀብቱም አይጸናም፤ ጥላውንም በምድር ላይ አይጥልም፤

30፤ ከጨለማ አይወጣም፤ ነበልባሉም ቅርንጫፎቹን ያደርቃቸዋል፥ አበባዎቹም ይረግፋሉ።

31፤ ዋጋው ከንቱ ነገር ይሆናልና ራሱን እያሳተ በከንቱ ነገር አይታመን።

32፤ ቀኑ ሳይደርስ ጊዜው ይፈጸማል፥ ቅርንጫፉም አይለመልምም።

33፤ እንደ ወይን ያልበሰለውን ዘለላ ያረግፋል፤ እንደ ወይራ አበባውን ይጥላል።

34፤ የዝንጉዎች ጉባኤ ሁሉ ለጥፋት ይሆናል፥ የጉቦ ተቀባዮችንም ድንኳን እሳት ትበላለች።

35፤ ጉዳትን ይፀንሳሉ፥ በደልንም ይወልዳሉ፥ ሆዳቸውም ተንኰልን ያዘጋጃል።