መጽሐፈ ኢዮብ። 28
1፤ በእውነት ብር የሚወጣበት፥ ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ።
2፤ ብረት ከመሬት ውስጥ ይወሰዳል፤ መዳብም ከድንጋይ ይቀለጣል።
3፤ ሰው ለጨለማ ፍጻሜን ያደርጋል፤ የጨለማውንና የሞት ጥላን ድንጋይ እስከ ወሰኑ ድረስ ይፈላልጋል።
4፤ ሰው ከሚኖርበት ርቀው መውረጃ ይቈፍራሉ፤ ከሰውም እግር ተረሱ፥ ከሰዎችም ርቀው እየተንጠለጠሉ ይወዛወዛሉ።
5፤ እንጀራ ከምድር ውስጥ ይወጣል፤ በእሳትም እንደሚሆን ታችኛው ይገለበጣል።
6፤ ድንጋይዋ የሰንፔር ስፍራ ነው፥ የወርቅም ድቃቂ አለው።
7፤ መንገድዋን ጭልፊት አያውቀውም፥ የአሞራም ዓይን አላየውም።
8፤ የትዕቢት ልጆች አልረገጡአትም፥ ደቦል አንበሳ አላለፈባትም።
9፤ ሰው ወደ ቡላድ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥ ተራራውንም ከመሠረቱ ይገለብጣል።
10፤ ከድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያ ይወቅራል፤ ዓይኑም ዕንቍን ሁሉ ታያለች።
11፤ ፈሳሹም እንዳይንጠባጠብ ይገድባል፤ የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።
12፤ ነገር ግን ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?
13፤ ሰው መንገድዋን አያውቅም፤ በሕያዋን ምድር አትገኝም።
14፤ ቀላይ። በእኔ ውስጥ የለችም ይላል፤ ባሕርም። በእኔ ዘንድ የለችም ይላል።
15፤ በምዝምዝ ወርቅ አትገኝም፥ ብርም ስለ ዋጋዋ አይመዘንም።
16፤ በኦፊር ወርቅ፥ በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም።
17፤ ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥ በጥሩ ወርቅም ዕቃ አትለወጥም።
18፤ ስለ ዛጐልና ስለ አልማዝ አይነገርም። የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ይበልጣል።
19፤ የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን አይተካከላትም፥ በጥሩም ወርቅ አትገመትም።
20፤ እንግዲያሳ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?
21፤ ከሕያዋን ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፥ ከሰማይ ወፎች ተሸሽጋለች።
22፤ ጥፋትና ሞት። ወሬዋን በጆሮቻችን ሰማን ብለዋል።
23፤ እግዚአብሔር መንገድዋን ያስተውላል፥ እርሱም ስፍራዋን ያውቃል።
24፤ እርሱም የምድርን ዳርቻ ይመለከታል፥ ከሰማይም በታች ያለውን ሁሉ ያያል።
25፤ ለነፋስ ሚዛንን ባደረገለት ጊዜ፥ ውኆችንም በስፍር በሰፈረ ጊዜ፥
26፤ ለዝናብም ሥርዓትን፥ ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን ባደረገ ጊዜ፥
27፤ በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፤ አዘጋጃትም፥ ደግሞም መረመራት።
28፤ ሰውንም። እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከኃጢአትም መራቅ ማስተዋል ነው አለው።