መጽሐፈ ኢዮብ። 26
1፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2፤ ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው! ብርታት የሌለውን ክንድ ምንኛ አዳንኸው!
3፤ ጥበብስ የሌለውን ምንኛ መከርኸው! ብዙ እውቀትንስ ምንኛ ገለጥህለት!
4፤ ይህንስ ቃል በማን እርዳታ ተናገርህ? የማንስ መንፈስ ከአንተ ዘንድ ወጣ?
5፤ ሙታን ሰዎች ከውኆች በታች፥ በውኆችም ውስጥ ከሚኖሩ በታች ይንቀጠቀጣሉ።
6፤ ሲኦል በፊቱ ራቁትዋን ናት፥ ለጥፋትም መጋረጃ የለውም።
7፤ ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፥ ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል።
8፤ ውኆችን በደመናዎቹ ውስጥ ያስራል፥ ደመናይቱም ከታች አልተቀደደችም።
9፤ የዙፋኑን ፊት ይከድናል፥ ደመናውንም ይዘረጋበታል።
10፤ ብርሃንና ጨለማ እስከሚለያዩበት ዳርቻ ድረስ፥ በውኆች ፊት ላይ ድንበርን አደረገ።
11፤ የሰማይ አዕማድ ይንቀጠቀጣሉ፥ ከተግሣጹም የተነሣ ይደነግጣሉ።
12፤ በኃይሉ ባሕርን ጸጥ ያደርጋል፥ በማስተዋሉም ረዓብን ይመታል።
13፤ በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ፥ እጁም በራሪይቱን እባብ ወጋች።
14፤ እነሆ፥ ይህ የመንገዱ ዳርቻ ብቻ ነው፤ ይህም የሰማነው ነገር ምንኛ ጥቂት ነው! የኃይሉንስ ነጐድጓድ ያስተውል ዘንድ ማን ይችላል?