ትንቢተ ሆሴዕ 9
1፤ እስራኤል ሆይ፥ ከአምላክህ ተለይተህ አመንዝረሃልና እንደ አሕዛብ ደስ አይበልህ፥ ሐሴትንም አታድርግ፤ በእህሉ አውድማ ሁሉ ላይ የግልሙትናን ዋጋ ወድደሃል።
2፤ አውድማውና መጥመቂያው አይመግባቸውም፥ ጉሽ ጠጅም ይጐድልባታል።
3፤ በእግዚአብሔር ምድር ላይ አይቀመጡም፤ ኤፍሬምም ወደ ግብጽ ይመለሳል፥ በአሦርም ርኩስን ነገር ይበላሉ።
4፤ ለእግዚአብሔርም የወይን ጠጅን ቁርባን አያፈስሱም፥ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤ የኀዘንም እንጀራ ይሆንላቸዋል፥ የሚበላውም ሁሉ ይረክሳል፤ እንጀራቸውም ለሰውነታቸው ይሆናል እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይገባም።
5፤ በዓመት በዓል ቀንና በእግዚአብሔር በዓል ቀን ምን ታደርጋላችሁ?
6፤ እነሆ፥ ከጥፋት ሸሽተው ሄዱ፥ ግብጽም ትሰበስባቸዋለች፥ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች፤ ሳማም የብራቸውን ጌጥ ይወርሳል፥ እሾህም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል።
7፤ የበቀል ወራት መጥቶአል፥ የፍዳም ወራት ደርሶአል፥ እስራኤልም ያውቃል፤ ከኃጢአትህና ከጠላትነትህ ብዛት የተነሣ ነቢዩ ሰንፎአል፥ መንፈስም ያለበት ሰው አብዶአል።
8፤ ኤፍሬም ከአምላኬ ጋር ተመልካች ነበረ፤ አሁን ግን ነቢዩ በመንገዱ ሁሉ ላይ የወፍ ወጥመድ ሆነ፥ በአምላኩም ቤት ጠላትነት አለ።
9፤ በጊብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፤ እርሱም በደላቸውን ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይበቀላል።
10፤ እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም ከመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በkWraት ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፥ ለነውርም ተለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥
11፤ የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም።
12፤ ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ ሰው እንዳይቀርላቸው ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፤ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው!
13፤ እኔ እንዳየሁ የኤፍሬም ልጆች ለምርኮ ተሰጥተዋል፤ ኤፍሬምም ልጆቹን ወደ ገዳዩች ያወጣል።
14፤ አቤቱ፥ ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፍን ማኅፀን የደረቀውንም ጡት ስጣቸው።
15፤ ክፋታቸው ሁሉ በጌልገላ አለ፤ በዚያ ጠልቻቸዋለሁ፤ ስለ ሠሩት ክፋት ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም፤ አለቆቻቸው ሁሉ ዓመፀኞች ናቸው።
16፤ ኤፍሬም ተመታ፥ ሥሩም ደረቀ፥ ፍሬም አያፈራም፤ ደግሞም ቢወልዱ የማኅፀናቸውን ፍሬ እገድላለሁ።
17፤ አልሰሙትምና አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተቅበዝባዦች ይሆናሉ።