ትንቢተ ሆሴዕ 10
1፤ እስራኤል ፍሬው የበዛለት የለመለመ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያውን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ማማር መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል።
2፤ ልባቸው ተከፈለ፤ አሁንም በደላቸውን ይሸከማሉ፤ እርሱ መሠዊያቸውን ያፈርሳል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል።
3፤ አሁንም። ንጉሥ የለንም፥ እግዚአብሔርን አልፈራንምና፤ ንጉሥስ ምን ያደርግልናል? ይላሉ።
4፤ የማይረባውን ቃል ይናገራሉ፤ ቃል ኪዳን በገቡ ጊዜ በሐሰት ይምላሉ፤ ስለዚህ መርዛም ሣር በእርሻ ትልም ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት ይበቅልባቸዋል።
5፤ የሰማርያ ሰዎች ስለ ቤትአዌን እምቦሳ ይፈራሉ፤ ክብሩም ከእርሱ ዘንድ ወጥቶአልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም በኀዘን ይንተባተባሉ።
6፤ ለንጉሡ ለኢያሪም እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ ወደ አሦር ይማረካል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል።
7፤ ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ ጠፍታለች።
8፤ የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾህና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፤ ተራሮችንም። ክደኑን፥ ኮረብቶችንም። ውደቁብን ይሉአቸዋል።
9፤ እስራኤል ሆይ፥ ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፤ በዚያ ጸንተዋል፤ በጊብዓ ላይ ሰልፍ አይደርስባቸውምን?
10፤ በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፤ ስለ ሁለቱም ኃጢአታቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ ይሰበሰቡባቸዋል።
11፤ ኤፍሬም ማበራየት እንደ ለመደች ጊደር ነው፥ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም አፈሩን ያለሰልሳል።
12፤ እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ።
13፤ ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና።
14፤ በሕዝብህም መካከል ሽብር ይነሣል፤ እናትም ከልጆችዋ ጋር በተፈጠፈጠች ጊዜ ሰልማን ቤትአርብኤልን በሰልፍ ቀን እንዳፈረሰ፥ አምባዎችህ ሁሉ ይፈርሳሉ።
15፤ ከኃጢአታችሁም ክፋት የተነሣ ቤቴል እንዲሁ ያደርግባችኋል፤ በነጋ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።