ትንቢተ ሆሴዕ 7
1፤ በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ።
2፤ እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንዳሰብሁ በልባቸው አያስቡም አሁንም ሥራቸው ከብባቸዋለች፥ በፊቴም አለች።
3፤ ንጉሡን በክፋታቸው፥ አለቆቹንም በሐሰታቸው ደስ አሰኝተዋል።
4፤ ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፤ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቆያል።
5፤ በንጉሣችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፤ እርሱም ከዋዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ።
6፤ እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፤ አበዛቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል።
7፤ ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም በሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፤ ከእነርሱም ወደ እኔ የሚጮኽ የለም።
8፤ ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው።
9፤ እንግዶች ጕልበቱን በሉት፥ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም።
10፤ የእስራኤልም ትዕቢቱ በፊቱ መሰከረ፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም።
11፤ ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌላት እንደ ሰነፍ ርግብ ነው፤ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ።
12፤ ሲሄዱ አሽክላዬን አዘረጋባቸዋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፤ መከራቸውን ሲሰሙ እገሥጻቸዋለሁ።
13፤ ከእኔ ፈቀቅ ብለዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐመፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ ልታደጋቸው ወደድሁ፥ እነርሱ ግን በሐሰት ተናገሩብኝ።
14፤ በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዐመፁ።
15፤ እኔም ክንዳቸውን አስተማርሁና አጸናሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን መከሩብኝ።
16፤ ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤ እንደ ተንኰለኛ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸው ከምላሳቸው ቍጣ የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።