ትንቢተ ሆሴዕ 14
1፤ እስራኤል ሆይ፥ በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ።
2፤ ከእናንተ ጋር ቃልን ውሰዱ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተመልሳችሁ። ኃጢአትን ሁሉ አስወግድ፥ በቸርነትም ተቀበለን፥ በወይፈንም ፋንታ የከንፈራችንን ፍሬ እንሰጣለን።
3፤ አሦር አያድነንም፤ በፈረስ ላይ አንቀመጥም፤ ድሀ አደጉም በአንተ ዘንድ ምሕረትን ያገኛልና ከእንግዲህ ወዲህ ለእጆቻችን ሥራ። አምላኮቻችን ናችሁ አንላቸውም በሉት።
4፤ ቍጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ዓመፃቸውን እፈውሳለሁ፥ በገዛ ፈቃዴ እወድዳቸዋለሁ።
5፤ ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፤ እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሩን ይሰድዳል።
6፤ ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፥ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል።
7፤ ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፤ ከእህሉም የተነሣ ይጠግባሉ፤ እንደ ወይንም አረግ ያብባሉ፤ መታሰቢያውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል።
8፤ ከእንግዲህ ወዲያ ጣዖት ለኤፍሬም ምንድር ነው? እኔ ሰምቼዋለሁ፥ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፤ ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል።
9፤ ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ፥ የሚያውቃትም አስተዋይ ማን ነው? የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው፥ ጻድቃንም ይሄዱበታል፤ ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታል።