ትንቢተ ሕዝቅኤል 4
1፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጡብን ወስደህ በፊትህ አኑራት የኢየሩሳሌምንም ከተማ ስዕል ሳልባት ክበባት፥
2፤ ምሽግም ሥራባት፥ አፈርም ደልድልባት፥ ሰፈርም አቁምባት፥ በዙሪያዋም የሚያፈርስ ግንድ አድርግባት።
3፤ የብረት ምጣድም ወስደህ በአንተና በከተማይቱ መካከል ለብረት ቅጥር አድርገው፥ ፊትህንም ወደ እርስዋ አቅና፥ የተከበበችም ትሆናለች አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።
4፤ አንተም በግራ ጐድንህ ተኛ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት አኑርባት፤ በምትተኛበትም ቀን ቍጥር ኃጢአታቸውን ትሸከማለህ።
5፤ እኔም የኃጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀን ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፤ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ።
6፤ እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ በቀኝ ጐድንህ ትተኛለህ፥ የይሁዳንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፤ አንድን ዓመት አንድ ቀን አድርጌ አርባ ቀን ሰጥቼሃለሁ።
7፤ ክንድህን ዕራቁቱን አድርገህ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ክቡ ታቀናለህ፥ ትንቢትም ትናገርባታለህ።
8፤ እነሆም፥ ገመድ አደርግብሃለሁ፥ የምትከበብበትንም ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከጐድን ጐድንህ አትገላበጥም።
9፤ አንተም ስንዴንና ገብስን ባቄላንና ምስርን ጤፍንና አጃን ወደ አንተ ውሰድ፥ በአንድ ዕቃም ውስጥ አድርገህ እንጀራ ጋግር፤ በጐድንህ እንደ ተኛህበት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ትበላዋለህ።
10፤ የምትበላውም በሚዛን በየቀኑ ሀያ ሀያ ሰቅል ይሁን፥ በየጊዜው ትበላዋለህ።
11፤ ውኃውንም በልክ የኢን መስፈሪያ ከስድስት እጅ አንድን እጅ ትጠጣለህ፥ በየጊዜው ትጠጣዋለህ።
12፤ እንደ ገብስ እንጐቻም አድርገህ ትበላዋለህ፥ ከሰውም በሚወጣ ፋንድያ በፊታቸው ትጋግረዋለሁ።
13፤ እግዚአብሔርም። እንዲሁ የእስራኤል ልጆች እነርሱን በምበትንባቸው በአሕዛብ መካከል ርኩስ እንጀራቸውን ይበላሉ አለ።
14፤ እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነሆ፥ ሰውነቴ አልረከሰችም፤ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጥንብና አውሬ የሰበረውን ከቶ አልበላሁም፥ ርኩስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም አልሁ።
15፤ እርሱም። እነሆ፥ በሰው ፋንድያ ፋንታ ኩበት ሰጥቼሃለሁ በእርሱም እንጀራህን ትጋግራለህ አለኝ።
16፤ ደግሞም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ የኢየሩሳሌምን እንጀራ በትር እሰብራለሁ፥ እየፈሩም እንጀራን በሚዛን ይበላሉ፥ እየደነገጡም ውኃን በልክ ይጠጣሉ፤
17፤ ይህም እንጀራንና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲደነቁ፥ በኃጢአታቸውም እንዲሰለስሉ ነው።