ትንቢተ ሕዝቅኤል 11
1፤ መንፈስም አነሣኝ፤ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደሚመለከት ወደ እግዚአብሔር ቤትም ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ። እነሆም፥ በበሩ መግቢያ ሀያ አምስት ሰዎች ነበሩ፥ በመካከላቸውም የሕዝቡን አለቆች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስ ልጅ ፈላጥያን አየሁ።
2፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ክፋትን የሚያስቡ በዚህችም ከተማ ክፉን ምክር የሚመክሩ ሰዎች ናቸው።
3፤ እነርሱም። በውኑ ቤቶችን የምንሠራበት ዘመን የቀረበ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት እኛም ሥጋ ነን ብለዋል።
4፤ ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገርባቸው፤ ትንቢት ተናገር።
5፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ወደቀብኝ እንዲህም አለኝ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህን ነገር ተናግራችኋል፥ እኔም የልባችሁን አሳብ አውቃለሁ።
6፤ በዚህች ከተማ ውስጥ ግዳዮቻችሁን አብዝታችኋል በጎዳናዎችዋም ግዳዮችን ሞልታችኋል።
7፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመካከልዋ ያኖራችኋቸው ግዳዮቻችሁ እነርሱ ሥጋው ናቸው፥ ይህችም ከተማ ድስቱ ናት፤ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ።
8፤ ሰይፍን ፈርታችኋል እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
9፤ ከመካከልዋም አወጣችኋለሁ፥ በእንግዶችም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ በላያችሁም ፍርድ አደርጋለሁ።
10፤ በሰይፍ ትወድቃላችሁ በእስራኤልም ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
11፤ ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፥ እኔም በእስራኤል ድንበር እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
12፤ በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አላደረጋችሁምና፤ በዙሪያችሁም እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል።
13፤ ትንቢትም በተናገርሁ ጊዜ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግምባሬ ተደፍቼ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! በውኑ የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን? ብዬ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ።
14፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
15፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ራቁ፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች የሚሉአቸው ወንድሞችህና ዘመዶችህ የወገኖችህም ሰዎች ሁሉ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ናቸው።
16፤ ስለዚህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ወደ አሕዛብ አርቄአቸዋለሁ፥ ወደ አገሮችም በትኛቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ፥ በመጡባቸው አገሮች በእነዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ በል።
17፤ ስለዚህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከአሕዛብ ዘንድ አከማቻችኋለሁ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች እሰበስባችኋለሁ፥ የእስራኤልንም ምድር እሰጣችኋለሁ።
18፤ ወደዚያም ይመጣሉ፥ ጸያፉንና ርኩሱንም ነገር ሁሉ ከእርስዋ ያወጣሉ።
19፤
20፤ በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ፥ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
21፤ ልባቸውም ጸያፍንና ርኩስን ነገር በሚከተል በእነርሱ ራስ ላይ መንገዳቸውን እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
22፤ ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ።
23፤ የእግዚአብሔርም ክብር ከከተማይቱ ውስጥ ተነሥቶ በከተማይቱ ምሥራቅ በኩል ባለው ተራራ ላይ ቆመ።
24፤ መንፈስም አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። ያየሁትም ራእይ ከእኔ ወጥቶ ተለየ።
25፤ እግዚአብሔርም ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞች ተናገርሁ።