0:00

ትንቢተ ሕዝቅኤል 19

1፤ አንተም በእስራኤል አለቆች ላይ ይህን ሙሾ አሙሽ፥ እንዲህም በል።

2፤ እናትህ ምን ነበረች? አንበሳ ነበረች፤ በአንበሶች መካከል ተጋደመች፤ በደቦል አንበሶች መካከል ግልገሎችዋን አሳደገች።

3፤ ከግልገሎችዋም አንዱን አወጣች እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፤ ንጥቂያንም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ።

4፤ አሕዛብም ወሬውን ሰሙ እርሱም በጕድጓዳቸው ተያዘ፥ በሰንሰለትም አድርገው ወደ ግብጽ ምድር ወሰዱት።

5፤ እርስዋም እንደ ደከመችና ተስፋዋ እንደ ጠፋ ባየች ጊዜ፥ ከግልገሎችዋ ሌላን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው።

6፤ እርሱም በአንበሶች መካከል ተመላለሰ ደቦል አንበሳም ሆነ፤ ንጥቂያም ተማረ፥ ሰዎችንም በላ።

7፤ ግንቦቻቸውንም አወቀ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረሰ፤ ከግሣቱም ድምፅ የተነሣ ምድሪቱና ሞላዋ ጠፋች።

8፤ አሕዛብም በዙሪያው ከየአገሩ ሁሉ ተሰበሰቡበት፤ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ በጕድጓዳቸውም ተያዘ።

9፤ በሰንሰለትም አድርገው በቀፎ ውስጥ አኖሩት ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ ድምፁም በእስራኤል ተራሮች ላይ ከዚያ ወዲያ እንዳይሰማ ወደ አምባ አገቡት።

10፤ እናትህ በመልክህ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ግንድ ነበረች፤ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና የምትሰፋ ሆነች።

11፤ ለእርስዋም ብርቱዎች በትሮች ነበሩአት እነርሱም ለነገሥታት በትሮች ነበሩ። ቁመታቸውም በዛፎች ቅርንጫፎች መካከል ረዘመ፥ በጫፎቻቸውም ብዛትና በርዝመታቸው ታዩ።

12፤ ነገር ግን በመዓት ተነቀለች ወደ መሬትም ተጣለች የምሥራቅም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፤ ብርቱዎች በትሮችዋም ተሰበሩና ደረቁ፥ እሳትም በላቻቸው።

13፤ አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማች መሬት ተተከለች።

14፤ ከጫፎችዋም በትሮች እሳት ወጣች ፍሬዋንም በላች፥ የነገሥታትም በትር ይሆን ዘንድ የበረታ በትር የለባትም። ይህ ሙሾ ነው፥ ለልቅሶም ይሆናል።