0:00

ትንቢተ ሕዝቅኤል 14

1፤ ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ።

2፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

3፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፤ እኔስ ከእነርሱ ልጠየቅን?

4፤

5፤ ስለዚህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁሉም በጣዖቶቻቸው ከእኔ ተለይተዋልና የእስራኤልን ቤት በልባቸው እይዝ ዘንድ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ ብለህ ንገራቸው።

6፤ ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ንስሐ ግቡ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ፊታችሁንም ከርኵሰታችሁ ሁሉ መልሱ።

7፤ ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ፥ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ፤

8፤ ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ ከሕዝቤም መካከል አጠፋዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

9፤ ነቢዩም ቢታለል ቃልንም ቢናገር፥ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እጄንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ ከሕዝቤም ከእስራኤል መካከል አጠፋዋለሁ።

10፤ ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ እንደሚጠይቀውም ሰው ኃጢአት እንዲሁ የነቢዩ ኃጢአት ይሆናል።

11፤ ይኸውም የእስራኤል ቤት ደግሞ ከእኔ ርቀው እንዳይስቱ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳይረክሱ ነው። እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

12፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

13፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ምድር በማመፅ በእኔ ላይ ኃጢአት ስትሠራ፥ እኔም እጄን ስዘረጋባት የእንጀራዋንም በትር ስሰብር ራብን ስሰድድባት ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ሳጠፋ፥

14፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች፥ ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም፥ ቢኖሩባት በጽድቃቸው የገዛ ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

15፤ ክፉዎቹን አራዊት በምድር ባሳልፍ እነርሱም ልጆችዋን ቢያጠፉ ስለ አራዊትም ማንም እንዳያልፍባት ባድማ ብትሆን፥

16፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ምድሪቱም ባድማ ትሆናለች፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

17፤ ወይም በዚያች ምድር ላይ ሰይፍ አምጥቼ። ሰይፍ ሆይ፥ በምድሪቱ ላይ እለፊ ብል፥ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ባጠፋ፥

18፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

19፤ ወይም በዚያች ምድር ላይ ቸነፈር ብሰድድ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ መዓቴን በደም ባፈስስባት፥

20፤ ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም ቢኖሩባት፥ እኔ ሕያው ነኝና በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

21፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ይልቁንስ ሰውንና እንስሳን ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ ፍርዶቼን፥ ሰይፍንና ራብን ክፉዎችንም አውሬዎች ቸነፈርንም፥ ስሰድድባት!

22፤ ነገር ግን፥ እነሆ፥ የሚያመልጡና ወንዶችና ሴቶች ልጆችን የሚያመጡ ይቀሩላታል፤ እነሆ፥ ወደ እናንተ ይወጣሉ እናንተም መንገዳቸውንና ሥራቸውን ታያላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ስላመጣሁት ክፉ ነገር ሁሉ ስላመጣሁባትም ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ።

23፤ መንገዳቸውንና ሥራቸውን ባያችሁ ጊዜ ያጽናኑአችኋል፤ ያደረግሁባትንም ሁሉ በከንቱ እንዳላደረግሁባት ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።