0:00

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ። 28

1፤ ዳዊትም የእስራኤልን አለቆች ሁሉ፥ የነገዶቹንም አለቆች፥ ንጉሡንም በክፍል የሚያገለግሉትን የጭፍሮች አለቆች፥ ሻለቆቹንም፥ የመቶ አለቆችንም፥ በንጉሥና በልጆች ሀብትና ግዛት ላይ የተሾሙትን፥ ጃንደረቦችንም፥ ጽኑዓን ኃይላኑንም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ።

2፤ ንጉሡም ዳዊት በእግሩ ቆሞ እንዲህ አለ። ወንድሞቼና ሕዝቤ ሆይ፥ ስሙኝ፤ ለእግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታቦትና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የዕረፍት ቤት ለመሥራት እኔ በልቤ አስቤአለሁ፤ ለሥራም የሚያስፈልገውን አዘጋጅቻለሁ፤

3፤ እግዚአብሔር ግን። የሰልፍ ሰው ነህና፥ ደምም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም ብሎኛል።

4፤ ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የዘላለም ንጉሥ እሆን ዘንድ ከአባቴ ቤት ሁሉ መርጦኛል፤ ይሁዳም አለቃ ይሆን ዘንድ መርጦታል፤ ከይሁዳም ቤት የአባቴን ቤት መርጦአል፤ ከአባቴም ልጆች መካከል በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሠኝ ዘንድ ሊመርጠኝ ወደደ።

5፤ እግዚአብሔርም ብዙ ልጆች ሰጥቶኛልና ከልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል።

6፤ እርሱም። ልጅ ይሆነኝ ዘንድ መርጬዋለሁና፥ እኔም አባት እሆነዋለሁና ልጅህ ሰሎሞን ቤቴንና አደባባዮቼን ይሠራል።

7፤ ትእዛዜንና ፈርዴንም በማድረግ እንደ ዛሬው ቢጸና መንግሥቱን ለዘላለም አጸናዋለሁ አለኝ።

8፤ አሁንም የእግዚአብሔር ጉባኤ እስራኤል ሁሉ እያዩ፥ አምላካችንም እየሰማ፥ ይህችን መልካሚቱን ምድር ትወርሱ ዘንድ፥ ለልጆቻችሁም ለዘላለም ታወርሱአት ዘንድ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ፥ ፈልጉም።

9፤ አንተም፥ ልጄ ሰሎሞን ሆይ፥ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና፥ የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል።

10፤ አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለመቅደስ የሚሆን ቤትን ትሠራ ዘንድ መርጦሃልና ጠንክረህ ፈጽመው።

11፤ ዳዊትም ለመቅደሱ ወለል፥ ለቤቱም፥ ለቤተ መዛግብቱም፥ ለደርቡና ለውስጡም ጓዳዎች፥ ለስርየቱም መክደኛ መቀመጫ ምሳሌውን ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው።

12፤ ደግሞም ለእግዚአብሔር ቤት አደባባዮችና በዙርያው ለሚሆኑ ጓዳዎች፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት፥ ለንዋየ ቅድሳቱም ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት በመንፈሱ ላሰበው ሁሉ ምሳሌን ሰጠው።

13፤

14፤ የካህናቱንና የሌዋውያኑንም ክፍላቸውን በእግዚአብሔርም ቤት በሚያገለግሉበት ሥራ ሁሉ አስታወቀው። በእግዚአብሔርም ቤት ለሚያገለግሉበት ዕቃ ሁሉ፥ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለወርቁ ዕቃ ወርቁን በሚዛን ሰጠው፤ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለብር ዕቃ ሁሉ ብሩን በሚዛን ሰጠው፤

15፤ ለወርቁም መቅረዞችና ለቀንዲሎችም ወርቁን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ ለብሩን መቅረዞች እንደ መቅረዙ ሁሉ ሥራ ሁሉ ብሩን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤

16፤ ለገጹ ኅብስት ገበታዎች ወርቁን በሚዛን ለገበታዎቹ ሁሉ፥ ብሩንም ለብሩ ገበታዎች ሰጠው፤

17፤ ለሜንጦቹና ለድስቶቹ ለመቅጃዎቹም ጥሩውን ወርቅ፥ ለወርቁም ጽዋዎች ወርቁን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን፥ ለብሩም ጽዋዎች ብሩን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን ሰጠው፤

18፤ ለዕጣኑም መሠዊዋ ጥሩውን ወርቅ በሚዛን፥ ክንፎቻቸውንም ዘርግተው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሸፈኑትን የኪሩቤልን የወርቅ ሰረገላ ምሳሌ ሰጠው።

19፤ ዳዊትም። የሥራውን ሁሉ ምሳሌ አውቅ ዘንድ ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር እጅ ተጽፎ መጣልኝ አለ።

20፤ ዳዊትም ልጁን ሰሎሞንን። ጠንክር፥ አይዞህ፥ አድርገውም፤ አምላኬ እግዚአብሔር አምላክ ከአንተ ጋር ነውና አትፍራ፥ አትደንግጥም፤ ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የሚሆነው ሥራ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ እርሱ አይተውህም፥ አይጥልህምም።

21፤ እነሆም፥ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ሁሉ የሚሆኑ የካህናትና የሌዋውያን ክፍሎች በዚህ አሉ፤ ለሁሉም ዓይነት አገልግሎትና ሥር በብልሃትና በነፍሱ ፈቃድ የሚሠራ ሁሉ ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አለቆችና ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው ይታዘዙሃል አለው።