0:00

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ። 22

1፤ ዳዊትም። ይህ የእግዚአብሔር ቤት ነው፥ ይህም ለእስራኤል ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ ነው አለ።

2፤ ዳዊትም በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ይሰበስቡ ዘንድ አዘዘ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ለመሥራት የሚወቀሩትን ድንጋዮች ይወቅሩ ዘንድ ጠራቢዎችን አኖረ።

3፤ ዳዊትም ለበሮቹ ሳንቃ ለሚሆኑ ለምስማርና ለመጠረቂያ ብዙ ብረት፥ ከብዛቱም የተነሣ የማይመዘን ናስ አዘጋጀ።

4፤ ሲዶናውያውንና የጢሮስ ሰዎች ብዙ የዝግባ እንጨት ወደ ዳዊት ያመጡ ነበርና ቍጥር ያሌላቸውን የዝግባ እንጨቶች አዘጋጀ።

5፤ ዳዊትም። ልጄ ሰሎሞን ታናሽና ለጋ ብላቴና ነው፥ ለእግዚአብሔርም የሚሠራው ቤት እጅግ ማለፊያና በአገሩ ሁሉ ስሙና ክብሩ እንዲጠራ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ስለዚህ አዘጋጅለታለሁ አለ። ዳዊትም ሳይሞት አስቀድሞ ብዙ አዘጋጀ።

6፤ ልጁንም ሰሎሞንን ጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ይሠራ ዘንድ አዘዘው።

7፤ ዳዊትም ሰሎሞንን እንዲህ አለ። ልጄ ሆይ፥ እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤት እሠራ ዘንድ በልቤ አስቤ ነበር።

8፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ። እጅግ ደም አፍስሰሃል፥ ታላቅም ሰልፍ አድርገሃል፤ በፊቴ በምድር ላይ ብዙ ደም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም።

9፤ እነሆ፥ የዕረፍት ሰው የሚሆን ልጅ ይወለድልሃል፤ በዙሪያው ካሉ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፈዋለሁ፤ ስሙ ሰሎሞን ይባላልና፥ በዘመኑም ሰላምንና ጸጥታን ለእስራኤል እሰጣለሁ።

10፤ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፥ ልጅም ይሆነኛል፥ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ የመንግሥቱንም ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።

11፤ አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም እንደ ተናገረው ያከናውንልህ፥ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ።

12፤ ብቻ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ሕግ ትጠብቅ ዘንድ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን ይስጥህ፥ በእስራኤልም ላይ ያሠልጥንህ።

13፤ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ሙሴን ያዘዘውን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ብትጠነቀቅ በዚያን ጊዜ ይከናወንልሃል፤ አይዞህ፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም።

14፤ አሁንም፥ እነሆ፥ በድህነቴ ለእግዚአብሔር ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፥ ሚዛንም የሌላቸው ብዙ ናስና ብረት አዘጋጀሁ፤ ደግሞም እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጀሁ፥ አንተም ከዚያ በላይ ጨምር።

15፤ በአንተም ዘንድ ብዙ ሠራተኞች፥ ድንጋይና እንጨት ወቃሪዎችና ጠራቢዎች፥ ሥራውንም ሁሉ ለማድረግ ጠቢባን ሰዎች ሁሉ አሉ።

16፤ የሚሠሩበት ወርቅና ብር ናስና ብረት ቍጥር የለውም፤ ተነሥተህ ሥራ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን።

17፤ ዳዊትም ደግሞ ልጁን ሰሎሞንን ያግዙ ዘንድ የእስራኤልን አለቆች ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው።

18፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይደለምን? በምድርም የሚቀመጡትን በእጄ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ምድርም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ፊት ተገዝታለችና በዙሪያችሁ ሁሉ ዕረፍትን ሰጥቶአችኋል።

19፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈልጉ ዘንድ ልባችሁንና ነፍሳችሁን ስጡ፤ ለእግዚአብሔርም ስም ወደሚሠራው ቤት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦትና የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ታመጡ ዘንድ ተነሥታችሁ የአምላክን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥሩ።