0:00

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ። 11

1፤ እስራኤልም ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው። እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤

2፤ አስቀድሞ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም። ሕዝቤን እስራኤልን አንተ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆናለህ 5ብሎህ ነበር አሉት።

3፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በሳሙኤልም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል በእስራኤል ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት።

4፤ ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባል ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ በአገሩም የተቀመጡ ኢያቡሳውያን በዚያ ነበሩ።

5፤ በኢያቡስም የተቀመጡ ዳዊትን። ወደዚህ አትገባም አሉት፤ ዳዊት ግን አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፤ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት።

6፤ ዳዊትም። ኢያቡሳውያንን አስቀድሞ የሚመታ ሰው አለቃና መኰንን ይሆናል አለ። የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ አስቀድሞ ወጣ፥ አለቃም ሆነ።

7፤ ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ ስለዚህም የዳዊት ከተማ ብለው ጠሩአት።

8፤ ከሚሎም ጀምሮ በዙሪያው ከተማ ሠራ፤ ኢዮአብም የቀረውን ከተማ አበጀ።

9፤ ዳዊትም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና እየበረታ ሄደ።

10፤ ለዳዊትም የነበሩት የኃያላን አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ስለ እስራኤል እንደ ተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ያነግሡት ዘንድ ከእስራኤል ሁሉ ጋር በመንግሥቱ ላይ አጸኑት።

11፤ የዳዊትም ኃያላን ቍጥር ይህ ነበረ፤ የሠላሳው አለቃ የአክሞናዊው ልጅ ያሾብአም ነበረ፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ ገደለ።

12፤ ከእርሱም በኋላ በሦስቱ ኃያላን መካከል የነበረ የአሆሃሂው የዱዲ ልጅ አልዓዛር ነበር።

13፤ እርሱ ከዳዊት ጋር በፈስደሚም ነበረ፥ በዚያም ገብስ በሞላበት እርሻ ውስጥ ፍልስጥኤማውያን ለሰልፍ ተሰብስበው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ።

14፤ በእርሻውም መካከል ቆመው ጠበቁት፥ ፍልስጥኤማውያንንም ገደሉ፤ እግዚአብሔርም በታላቅ ማዳን አዳናቸው።

15፤ ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓለቱ ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር።

16፤ በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በቤተ ልሔም ነበረ።

17፤ ዳዊትም። በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ማን ይሰጠኛል? ብሎ ተመኘ።

18፤ እነዚህም ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፥ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፥ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ።

19፤ ይህን አደርግ ዘንድ አምላኬ ይከልክለኝ፤ በነፍሳቸው የደፈሩትም እነዚህ ሰዎች ደም እጠጣለሁን? በነፍሳቸው አምጥተውታል አለ። ስለዚህም ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱም ኃያላን ያደረጉት ይህ ነው።

20፤ የኢዮአብም ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ፤ ጦሩንም በሦስት መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፥ በሦስቱም መካከል ስሙ የተጠራ ነበረ።

21፤ በሁለተኛውም ተራ በሆኑት በሦስቱ መካከል የከበረ ነበረ፥ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም።

22፤ በቀብስኤልም የነበረው፥ ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊን የአሪኤል ሁለቱን ልጆች ገደለ፤ በአመዳይም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ።

23፤ ቁመቱም አምስት ክንድ የነበረውን ረጅሙን ግብጻዊውን ሰው ገደለ፤ በግብጻዊውም እጅ የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር ነበረ፤ እርሱ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፥ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነቅሎ በገዛ ጦሩ ገደለው።

24፤ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኃያላን መካከል የተጠራ ነበር።

25፤ እነሆ፥ ከሠላሳው ይልቅ የከበረ ነበረ፥ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በዘበኞቹ ላይ ሾመው።

26፤ ደግሞም በጭፍሮች ዘንድ የነበሩት ኃያላን እነዚህ ናቸው፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተ ልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥

27፤ ሃሮራዊው ሳሞት፥ ፈሎናዊው ሴሌስ፥

28፤ የቴቁሔ ሰው የዒስካ ልጅ ዒራስ፥

29፤ ዓናቶታዊው አቢዔዜር፥ ኩሳታዊው ሴቤካይ፥

30፤ አሆሃዊው ዔላይ፥ ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፥

31፤ ከብንያም ወገን ከግብዓ የሪባይ ልጅ ኤታይ፥

32፤ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ የገዓስ ወንዝ ሰው ኡሪ፥

33፤ ዓረባዊው አቢኤል፥ ባሕሩማዊው ዓዝሞት፥

34፤ ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፥ የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፥

35፤ የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥

36፤ የኡር ልጅ ኤሊፋል፥ ሚኬራታዊው ኦፌር፥

37፤ ፍሎናዊው አኪያ፥ ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፥

38፤ የናታንም ወንድም ኢዮኤል፥ የሐግሪ ልጅ ሚብሐር፥

39፤ አሞናዊው ጼሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ነሃራይ፥

40፤ ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው ጋሬብ፥

41፤ ኬጢያዊው ኦርዮ፥ የአሕላይ ልጅ ዛባድ፥

42፤ የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፥ እርሱ የሮቤላውያን አለቃ ነበረ፥

43፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሰዎች ነበሩ፥ የማዕካ ልጅ ሐናን፥ ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፥

44፤ አስታሮታዊው ዖዝያ፥ የአሮኤራዊው የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፥

45፤ የሽምሪ ልጅ ይድኤል፥ ወንድሙም ይድኤል፥ ወንድሙም ቲዳዊው ዮሐ፥

46፤ መሐዋዊው ኤሊኤል፥ ይሪባይ፥ ዮሻዊያ፥ የኤልናዓም ልጆች፥ ሞዓባዊው ይትማ፥

47፤ ኤልኤል፥ ዖቤድ፥ ምጾባዊው የዕሢኤል።