ኦሪት ዘፍጥረት 50
1፤ ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፥ በእርሱም ላይ አለቀሰ፥ ሳመውም።
2፤ ዮሴፍም ባለመድኃኒቶች አገልጋዮቹ አባቱን በሽቱ ያሹት ዘንድ አዘዘ፤ ባለመድኃኒቶችም እስራኤልን በሽቱ አሹት።
3፤ አርባ ቀንም ፈጸሙለት፤ የሽቱ መደረጊያው ወራት እንደዚሁ ይፈጸማልና፤ የግብፅም ሰዎች ሰባ ቀን አለቀሱለት።
4፤ የልቅሶውም ወራት ባለፈ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን ቤተ ሰቦች እንዲህ ብሎ ተናገረ። እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት።
5፤ አባቴ አምሎኛል እንዲህ ሲል። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር ከዚያ ቅበረኝ። አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ።
6፤ ፈርዖንም። ውጣ፥ አባትህንም እንዳማለህ ቅበረው አለው።
7፤ ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፤ የፈርዖን ሎላልትም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችም የግብፅ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ፤
8፤ የዮሴፍም ቤተ ሰቦች ሁሉ ወንድሞቹም የአባቱም ቤተ ሰቦች ወጡ፤ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን ብቻ በጌሤም ተዉ።
9፤ ሰረገሎችም ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፥ ሠራዊቱም እጅግ ብዙ ነበረ።
10፤ በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ መጡ፥ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፤ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት።
11፤ በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ። ይህ ለግብፅ ሰዎች ታላቅ ልቅሶ ነው አሉ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ብለው ጠሩት፤ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው።
12፤ ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፤
13፤ ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት፥ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፤ እርስዋም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት።
14፤ ዮሴፍና ወንድሞቹ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብፅ ተመለሱ።
15፤ የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሉ። ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።
16፤ ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት። አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል።
17፤ ዮሴፍን እንዲህ በሉት። እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፥ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፤ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል።
18፤ ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው። እነሆ እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን አሉት።
19፤ ዮሴፍም አላቸው። አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን?
20፤ እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው።
21፤ አሁንም አትፍሩ፤ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ። አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም።
22፤ ዮሴፍም በግብፅ ተቀመጠ፥ እርሱና የአባቱም ቤተ ሰብ፤ ዮሴፍም መቶ አሥር ዓመት ኖረ።
23፤ ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ፤ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ።
24፤ ዮሴፍም ወንድሞቹን አለ። እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፥ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል።
25፤ ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች። እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ አማላቸው።
26፤ ዮሴፍም በመቶ አሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ፤ በሽቱም አሹት፥ በግብፅ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።