ኦሪት ዘፍጥረት 25
1፤ አብርሃምም ደግሞ ስምዋ ኬጡራ የተባላች ሚስት አገባ።
2፤ እርስዋም ዘምራንን፥ ዮቅሳንን፥ ሜዳንን፥ ምድያምን፥ የስቦቅን፥ ስዌሕን ወለደችለት።
3፤ ዮቅሳንም ሳባንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች አሦርያውያን፥ ለጡሳውያን፥ ለኡማውያን ናቸው።
4፤ የምድያምም ልጆች ጌፌር፥ ዔፌር፥ ሄኖኅ፥ አቢዳዕ፥ ኤልዳዓ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው።
5፤ አብርሃምም የነበረውን ሁሉ ለይስሐቅ ሰጠው፤
6፤ የአብርሃምም ለነበሩ ለቁባቶቹ ልጆች አብርሃም ስጦታን ሰጣቸው፤ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ፀሐይ መውጫ ወደ ምሥራቅ አገር ሰደዳቸው።
7፤ አብርሃምም የኖረበት የዕድሜው ዓመታት እነዚህ ናቸው፤ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ።
8፤ አብርሃምም ነፍሱን ሰጠ፥ በመልካም ሽምግልናም ሞተ፤ ሸመገለም፥ ብዙ ዘመንም ጠገበ፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።
9፤ ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤልም በመምሬ ፊት ለፊት ባለው በኬጢያዊ በሰዓር ልጅ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት ።
10፤ አብርሃም ከኬጢ ልጆች የገዛው እርሻ ይህ ነው፤ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ።
11፤ አብርሃምም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ።
12፤ የሣራ ባሪያ ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችው የአብርሃም ልጅ የእስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤
13፤ የእስማኤልም የልጆቹ ስም በየስማቸውና በየትውልዳቸው እንዲህ ነው፤ የእስማኤል የበኵር ልጁ
14፤ ነባዮት፥ ቄዳር፥ ነብዳኤል፥ መብሳም፥ ማስማዕ፥
15፤ ዱማ፥ ማሣ፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ኢጡር፥ ናፌስ፥ ቄድማ።
16፤ የእስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፥ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይኸው ነው፤ በየወገናቸውም አሥራ ሁለት አለቆች ናቸው።
17፤ እስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው፤ ነፍሱን ሰጠ ሞተም፤ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።
18፤ መኖሪያቸውም ከኤውላጥ አንሥቶ በግብፅ ፊት ለፊት እስከምትገኝ እስከ ሱር ድረስ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ ላይ ነበረ፤ እንዲህም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ተቀመጠ።
19፤ የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤
20፤ ይስሐቅም አርባ ዓመት ሲሆነው ርብቃን አገባ፤ እርስዋም በሁለት ወንዞች መካከል ያለ የሶርያዊው የባቱኤል ልጅና የሶርያዊው የላባ እኅት ናት።
21፤ ይስሐቅም ስለሚስቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ መካን ነበረችና፤ እግዚአብሔርም ተለመነው፥ ርብቃም ሚስቱ ፀነሰች።
22፤ ልጆችም በሆድዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርስዋም። እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔ ምኔ ነው? አለች። ከእግዚአብሔርም ትጠይቅ ዘንድ ሄደች።
23፤ እግዚአብሔርም አላት። ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው፥ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል።
24፤ ትወልድ ዘንድ ዘመንዋ በተፈጸመ ጊዜም፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ።
25፤ በፊትም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጕር ለብሶ ነበር፤ ስሙም ዔሳው ተባለ።
26፤ ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙም ያዕቆብ ተባለ። እርስዋ ልጆችን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር።
27፤ ብላቴኖቹም አደጉ፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር።
28፤ ይስሐቅም ዔሳውን ይወድ ነበር፥ ካደነው ይበላ ነበርና፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበረች።
29፤ ያዕቆብም ወጥ ሠራ፤ ዔሳውም ደክሞ ከበረሃ ገባ፤
30፤ ዔሳውም ያዕቆብን። ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ ደክሜአለሁና አለው፤ ስለዚህ ስሙ ኤዶም ተባለ።
31፤ ያዕቆብም። በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ አለው።
32፤ ዔሳውም። እነሆ፥ እኔ ልሞት ነኝ፤ ይህች ብኵርና ለምኔ ናት? አለ ።
33፤ ያዕቆብም። እስኪ በመጀመሪያ ማልልኝ አለው። ማለለትም፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠ።
34፤ ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ወጥ ሰጠው፤ በላ፥ ጠጣ፥ ተነሥቶም ሄደ፤ እንዲሁም ዔሳው ብኵርናውን አቃለላት።