ኦሪት ዘፍጥረት 11
1፤ ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች።
2፤ ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ።
3፤ እርስ በርሳቸውም። ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም እንተኵሰው ተባባሉ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው፤ የምድርም ዝፋት እንደ ጭቃ ሆነችላቸው።
4፤ እንዲህም። ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ።
5፤ እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ።
6፤ እግዚአብሔርም አለ። እነሆ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፥ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም።
7፤ ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።
8፤ እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተዉ።
9፤ ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል።
10፤ የሴም ትውልድ ይህ ነው። ሴም የመቶ ዓመት ሰው ነበረ፥ አርፋክስድንም ከጥፋት ውኃ በኋላ በሁለተኛው ዓመት ወለደ።
11፤ ሴምም አርፋክስድን ከወለደ በኋላ አምስት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
12፤ አርፋክስድም መቶ ሠላሳ አምስት ዓመት ኖረ፥ ቃይንምንም ወለደ፤
13፤ አርፋክስድም ቃይንምን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም። ቃይንምም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ሳላንም ወለደ፤ ቃይንምም ሳላን ከወለደ በኋላ ሶስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
14፤ ሳላም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ዔቦርንም ወለደ፤
15፤ ሳላም ዔቦርን ከወለደ በኋላ ሦስት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
16፤ ዔቦርም መቶ ሠላሳ አራት ዓመት ኖረ፥ ፋሌቅንም ወለደ፤
17፤ ዔቦርም ፋሌቅን ከወለደ በኋላ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
18፤ ፋሌቅም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ራግውንም ወለደ፤
19፤ ራግውንም ከወለደ በኋላ ፋሌቅ ሁለት መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
20፤ ራግውም መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ሴሮሕንም ወለደ፤
21፤ ራግውም ሴሮሕን ከወለደ በኋላ ሁለት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
22፤ ሴሮሕም መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ናኮርንም ወለደ፤
23፤ ናኮርንም ከወለደ በኋላ ሴሮሕ ሁለት መቶ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
24፤ ናኮርም መቶ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ታራንም ወለደ፤
25፤ ታራንም ከወለደ በኋላ ናኮር መቶ ሃያ ዘጠኝ ዓመት ኖረ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም ወለደ፤ ሞተም።
26፤ ታራም መቶ ዓመት ኖረ፥ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ።
27፤ የታራም ትውልድ እነሆ ይህ ነው። ታራ አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ፤ ሐራንም ሎጥን ወለደ።
28፤ ሐራንም በተወለደበት አገር በከለዳውያን ዑር በአባቱ በታራ ፊት ሞተ።
29፤ አብራምና ናኮርም ሚስቶችን አገቡ፤ የአብራም ሚስት ስምዋ ሦራ ነው፤ የናኮር ሚስት የሐራን ልጅ ሚልካ ናት፤ ሐራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነው።
30፤ ሦራም መካን ነበረች፤ ልጅ አልነበራትም።
31፤ ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥን የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ወሰደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ፤ ወደ ካራንም መጡ፥ ከዚያም ተቀመጡ።
32፤ የታራም ዕድሜ ሁለት መቶ አምስት ዓመት ሆነ፤ ታራም በካራን ሞተ።