ትንቢተ አሞጽ 6
1፤ በጽዮን ላሉ ዓለመኞች፥ በሰማርያም ተራራ ላይ ተዘልለው ለተቀመጡ፥ የእስራኤልም ቤት ወደ እነርሱ ለመጡባቸው ለአሕዛብ አለቆች ወዮላቸው!
2፤ ወደ ካልኔ አልፋችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይሻላሉን? ወይስ ድንበራቸው ከድንበራችሁ ይሰፋልን?
3፤ ክፉውን ቀን ከእናንተ ለምታርቁ፥ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ፥
4፤ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፥ በምንጣፋችሁም ላይ ተደላድላችሁ ለምትቀመጡ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፥
5፤ በመሰንቆም ድምፅ ለምትንጫጩ፥ እንደ ዳዊትም የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፥
6፤ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፥ እጅግ ባማረ ሽቱም ለምትቀቡ፥ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችሁ!
7፤ ስለዚህ በምርኮ መጀመሪያ ይማረካሉ፥ ተደላድለው ከተቀመጡትም ዘንድ ዘፈን ይርቃል።
8፤ ጌታ እግዚአብሔር። የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ አዳራሾቹንም ጠልቻለሁ፤ ስለዚህ ከተማይቱንና የሚኖሩባትን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ ብሎ በራሱ ምሎአል፥ ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር።
9፤ እንዲህም ይሆናል፤ አሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ።
10፤ አጥንቱንም ከቤቱ ያወጡ ዘንድ የሰው ዘመድና አቃጣዩ ባነሡት ጊዜ፥ በቤቱም ውስጥ ያለውን። እስከ አሁን ድረስ ገና ሰው በአንተ ዘንድ አለን? ባለው ጊዜ፥ እርሱም። ማንም የለም ባለ ጊዜ፤ ያን ጊዜ። የእግዚአብሔርን ስም እንጠራ ዘንድ አይገባንምና ዝም በል ይለዋል።
11፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ያዝዛል፤ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል።
12፤
13፤ ፍርድን ወደ ሐሞት፥ የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት የለወጣችሁ፥ በከንቱም ነገር ደስ የሚላችሁ። በኃይላችን ቀንድ የወሰድን አይደለምን? የምትሉ፥ እናንተ ሆይ፥ በውኑ ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይጋልባሉን? ወይስ በሬዎች በዚያ ላይ ያርሳሉን?
14፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ ሕዝብን አስነሣባችኋለሁ፥ ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር፤ እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዓረባ ወንዝ ድረስ ያስጨንቋችኋል።