ትንቢተ አሞጽ 5

1፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእናንተ ላይ ለሙሾ የማነሣውን ይህን ቃል ስሙ።

2፤ የእስራኤል ድንግል ወደቀች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሣም፤ በምድርዋ ላይ ተጣለች፥ የሚያስነሣትም የለም።

3፤ ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላልና። ሺህ ከሚወጣባት ከተማ መቶ ይቀርላታል፥ መቶም ከሚወጣባት ከተማ ለእስራኤል ቤት አሥር ይቀርላታል።

4፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላልና። እኔን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤

5፤ ነገር ግን ጌልገላ ፈጽሞ ትማረካለችና፥ ቤቴልም ከንቱ ትሆናለችና ቤቴልን አትፈልጉ፥ ወደ ጌልገላም አትግቡ፥ ወደ ቤርሳቤህም አትለፉ።

6፤ በዮሴፍ ቤት እሳት እንዳትቃጠል፥ በቤቴል የሚያጠፋትም ሳይኖር እንዳትበላ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ።

7፤ ፍርድን ወደ እሬት የምትለውጡ፥ ጽድቅንም በምድር ላይ የምትጥሉ እናንተ ሆይ፥

8፤ ሰባቱን ከዋክብትና ኦሪዮን የተባለውን ኮከብ የፈጠረውን፥ የሞትን ጥላ ወደ ንጋት የሚለውጠውን፥ ቀኑንም በሌሊት የሚያጨልመውን፥ የባሕሩንም ውኆች ጠርቶ በምድር ፊት ላይ የሚያፈስሳቸውን፥

9፤ አምባውም እንዲፈርስ በብርቱ ላይ የድንገት ጥፋት የሚያመጣውን ፈልጉ፤ ስሙ እግዚአብሔር ነው።

10፤ በበሩ አደባባይ የሚገሥጸውን ጠሉ፥ እውነትም የሚናገረውን ተጸየፉ።

11፤ ድሀውንም ደብድባችኋልና፥ የስንዴውንም ቀረጥ ከእርሱ ወስዳችኋልና ከተጠረበ ድንጋይ ቤቶችን ሠርታችኋል፥ ነገር ግን አትቀመጡባቸውም፤ ያማሩ የወይን ቦታዎች ተክላችኋል፥ ነገር ግን ከወይን ጠጃቸው አትጠጡም።

12፤ ጻድቁን የምታስጨንቁ፥ ጉቦንም የምትቀበሉ፥ በበሩም አደባባይ የችጋረኛውን ፍርድ የምታጣምሙ እናንተ ሆይ፥ በደላችሁ እንዴት እንደ በዛ፥ ኃጢአታችሁም እንዴት እንደ ጸና እኔ አውቃለሁና።

13፤ ስለዚህ ክፉ ዘመን ነውና በዚያ ዘመን አስተዋይ የሚሆን ዝም ይላል።

14፤ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ መልካሙን እንጂ ክፉውን አትፈልጉ፤ እንዲህም እናንተ እንደ ተናገራችሁ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል።

15፤ ክፉውን ጥሉ፥ መልካሙንም ውደዱ፥ በበሩም አደባባይ ፍርድን አጽኑ፤ ምናልባት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ለዮሴፍ ቅሬታ ይራራ ይሆናል።

16፤ ስለዚህ ጌታ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በየአደባባዩ ሁሉ ላይ ዋይታ ይሆናል፤ በየመንገዱም ሁሉ ላይ ወዮ ወዮ ይባላል፤ ገበሬዎቹም ወደ ልቅሶ፥ አልቃሾቹም ወደ ዋይታ ይጠራሉ።

17፤ በመካከልህ አልፋለሁና በወይኑ ቦታ ሁሉ ልቅሶ ይሆናል፥ ይላል እግዚአብሔር።

18፤ የእግዚአብሔርን ቀን ለምትፈልጉ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።

19፤ ከአንበሳ ፊት እንደ ሸሸ ድብም እንዳገኘው ሰው፥ ወይም ወደ ቤት ገብቶ እጁን በግድግዳ ላይ እንዳስደገፈና እባብ እንደ ነደፈው ሰው ነው።

20፤ የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?

21፤ ዓመት በዓላችሁን ጠልቼዋለሁ ተጸይፌውማለሁ፤ የተቀደሰውም ጉባኤአችሁ ደስ አያሰኘኝም።

22፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁና የእህሉን ቍርባናችሁን ብታቀርቡልኝም እንኳ አልቀበለውም፤ ለምስጋና መሥዋዕት የምታቀርቡልኝን የሰቡትን እንስሶች አልመለከትም።

23፤ የዝማሬህንም ጩኸት ከእኔ ዘንድ አርቅ፤ የመሰንቆህንም ዜማ አላደምጥም።

24፤ ነገር ግን ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ።

25፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በውኑ በምድረ በዳ አርባ ዓመት ሙሉ መሥዋዕትንና ቍርባንን አቅርባችሁልኛልን?

26፤ ለራሳችሁም የሠራችኋቸውን ምስሎች፥ የሞሎክን ድንኳንና የአምላካችሁን የሬፋን ኮከብ አነሣችሁ።

27፤ ስለዚህ ከደማስቆ ወደዚያ አስማርካችኋለሁ፥ ይላል ስሙ የሠራዊት አምላክ የተባለ እግዚአብሔር።