መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 6

1፤ አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከአንቺ ጋር እንፈልገው ዘንድ ውድሽ ወዴት ሄደ? ውድሽስ ወዴት ፈቀቅ አለ?

2፤ ውዴ በገነቱ መንጋውን ያሰማራ ዘንድ አበባውንም ይሰበስብ ዘንድ ወደ ሽቱ መደብ ወደ ገነቱ ወረደ።

3፤ እኔ የወዴ ነኝ ውዴም የእኔ ነው፤ በሱፉ አበባ መካከል መንጋውን ያሰማራል።

4፤ ወዳጄ ሆይ፥ እንደ ቴርሳ ውብ ነሽ፥ እንደ ኢየሩሳሌምም ያማርሽ ነሽ፤ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት ታስፈሪያለሽ።

5፤ አውከውኛልና ዓይኖችሽን ከፊቴ መልሺ፤ ጠጕርሽ ከገለዓድ እንደ ወረደ እንደ ፍየል መንጋ ነው።

6፤ ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ወጡ ሁሉ መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው።

7፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጕንጭና ጕንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው።

8፤ ስድሳ ንግሥታት ሰማንያም ቍባቶች ቍጥር የሌላቸውም ቈነጃጅት አሉ።

9፤ ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው አሞገሱአት፥ ንግሥታትና ቍባቶችም አመሰገኑአት።

10፤ ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ፥ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች፥ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት?

11፤ የወንዙን ዳር ልምላሜ አይ ዘንድ፥ ወይኑ አብቦ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እመለከት ዘንድ ወደ ገውዝ ገነት ወረድሁ።

12፤ ሳላውቅ ነፍሴ በከበረው ሰረገላ ላይ አስቀመጠችኝ።

13