መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 1
1፤ ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር።
2፤ በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና።
3፤ ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው፤ ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው፤ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ።
4፤ ሳበኝ፥ ከአንተም በኋላ እንሮጣለን፤ ንጉሡ ወደ ቤቱ አገባኝ በአንተ ደስ ይለናል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን፤ በቅንነት ይወድዱሃል።
5፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች።
6፤ ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና፤ ጥቁር ስለ ሆንሁ አትዩኝ፤ የእናቴ ልጆች ተጣሉኝ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፤ ነገር ግን የእኔን ወይን ቦታ አልጠበቅሁም።
7፤ ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፤ ወዴት ታሰማራለህ? በቅትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ?
8፤ አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደ ሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ።
9፤ ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረስ መሰልሁሽ።
10፤ የጕንጭሽ ውበት በከበረ ሉል፥ አንገትሽም በዕንቍ ድሪ ያማረ ነው።
11፤ ባለ ብር ጕብጕብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም እናደርግልሻለን።
12፤ ንጉሡ በማዕዱ ሳለ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ።
13፤ ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው።
14፤ ውዴ ለእኔ በዓይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ እቅፍ ነው።
15፤ ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ ዓይኖችሽም እንደ ርግቦች ናቸው።
16፤ ውዴ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፤ አልጋችንም ለምለም ነው።
17፤ የቤታችን ሰረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው።