መጽሐፈ ዕዝራ። 8
1፤ በንጉሡ በአርጤክስስ መንግሥት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የወጡ የአባቶች ቤቶች አለቆች እነዚህ ናቸው ትውልዳቸውም ይህ ነው፤
2፤ ከፊንሐስ ልጆች ጌርሶን፥ ከኢታምር ልጆች ዳንኤል፥ ከዳዊት ልጆች ሐጡስ፥ ከሴኬንያ ልጆች፥
3፤ ከፋሮስ ልጆቾ ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር መቶ አምሳ ወንዶች በትውልድ ተቈጠሩ።
4፤ ከፋሐት ሞዓብ ልጆች የዘራእያ ልጅ ኤሊሆዔናይ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ወንዶች።
5፤ ከሴኬንያ ልጆች የየሕዚኤል ልጅ፥ ከእርሱም ጋር ሦስት መቶ ወንዶች።
6፤ ከዓዲን ልጆች የዮናታን ልጅ ዔቤድ፥ ከእርሱም ጋር አምሳ ወንዶች።
7፤ ከኤላም ልጆች የጎቶልያ ልጅ የሻያ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ወንዶች።
8፤ የሰፋጥያስ ልጆች የሚካኤል ልጅ ዝባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሰማንያ ወንዶች።
9፤ ከኢዮአብ ልጆች የይሒኤል ልጅ አብድዩ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ አሥራ ስምንት ወንዶች።
10፤ ከሰሎሚት ልጆች የዮሲፍያ ልጅ፥ ከእርሱም ጋር መቶ ስድሳ ወንዶች።
11፤ ከቤባይ ልጆች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር ሀያ ስምንት ወንዶች።
12፤ ከዓዝጋድ ልጆች የሃቃጣን ልጅ ዮሐናን፥ ከእርሱም ጋር መቶ አሥር ወንዶች።
13፤ ከኋለኞቹ ከአዶኒቃም ልጆች ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፋላት፥ ይዑኤል፥ ሸማያ፥ ከእነርሱም ጋር ስድሳ ወንዶች።
14፤ ከበጉዋይ ልጆች ዑታይና ዘቡድ፥ ከእነርሱም ጋር ሰባ ወንዶች።
15፤ ወደ አኅዋም ወደሚፈስስ ወንዝ ሰበሰብኋቸው፥ በዚያም ሦስት ቀን ሰፈርን፤ ሕዝቡንና ካህናቱን ስቈጥራቸው በዚያ ከሌዊ ልጆች ማንንም አላገኘሁም።
16፤ ወደ አለቆቹም ወደ አልዓዛር፥ ወደ አርኤል፥ ወደ ሸማያ፥ ወደ ኤልናታን፥ ወደ ያሪብ፥ ወደ ኤልናታን፥ ወደ ናታን፥ ወደ ዘካርያስ፥ ወደ ሜሱላም፥ ደግሞም ወደ አዋቂዎቹ ወደ ዮያሪብና ወደ ኤልናታን ላክሁ።
17፤ በካሲፍያ ስፍራ ወደ ነበረው ወደ አለቃው ወደ አዶ ላክኋቸው፤ ለአምላካችን ቤት አገልጋዮችን ያመጡልን ዘንድ በካሲፍያ ስፍራ ለሚኖሩት ለአዶና ለወንድሞቹ ለናታኒም የሚነግሩአቸውን በአፋቸው አደረግሁ።
18፤ በላያችንም መልካም በሆነው በአምላካችን እጅ ከእስራኤል ልጅ ከሌዊ ልጅ ከሞሖሊ ልጆች ወገን የነበረውን አስተዋይ ሰው ሰራብያን፥ ከእርሱም ጋር አሥራ ስምንቱን ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን።
19፤ ደግሞም ሐሸብያን ከእርሱም ጋር ከሜራሪ ልጆች ወገን የነበረውን የሻያንና ሀያውን ወንድሞቹንና ልጆቻቸውን።
20፤ ሌዋውያንንም እንዲያገለግሉ ዳዊትና አለቆቹ ከሰጡአቸው ናታኒም ውስጥ ሁለት መቶ ሀያ ናታኒም አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በስም በስማቸው ተጠሩ።
21፤ በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ።
22፤ ንጉሡንም። የአምላካችን እጅ በሚሹት ሁሉ ላይ ለመልካም ነው፤ ኃይሉና ቍጣው ግን እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ነው ብለን ተናግረን ነበርና በመንገድ ካለው ጠላት ያድኑን ዘንድ ጭፍራና ፈረሰኞች ከንጉሡ እለምን ዘንድ አፍሬ ነበርና።
23፤ ስለዚህም ነገር ጾምን፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመንን፤ እርሱም ተለመነን።
24፤ ከካህናቱም አለቆች አሥራ ሁለት ሰዎችን፥ ሰራብያንና ሐሸቢያን ከእነርሱም ጋር አሥር ወንድሞቻቸውን ለየሁ፤
25፤ ንጉሡና አማካሪዎቹ አለቆቹም በዚያም የተገኙት እስራኤል ሁሉ ያቀረቡትን ለአምላካችን ቤት የቀረበውን ብሩንና ወርቁን ዕቃውንም መዝኜ ሰጠኋቸው።
26፤ ስድስት መቶ አምሳ መክሊት ብር፥ አንድ መቶም መክሊት የብር ዕቃዎች፥ አንድ መቶም መክሊት ወርቅ፥
27፤ ሀያም ባለሺህ ዳሪክ የወርቅ ጽዋዎች፥ ሁለትም እንደ ወርቅ የከበሩ ከጥሩ ከሚያንጸባርቅ ናስ የተሠሩ ዕቃዎች መዝኜ በእጃቸው ሰጠሁ።
28፤ እኔም። እናንተ ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፥ ዕቃዎቹም ቅዱስ ናቸው፤ ብሩና ወርቁም ለአባቶቻችን አምላክ ለእግዚአብሔር በፈቃድ የቀረበ ነው፤
29፤ በካህናትና በሌዋውያን አለቆች በእስራኤልም አባቶች ቤቶች አለቆች ፊት በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ቤት ጓዳዎች ውስጥ እስክትመዝኑ ድረስ ተግታችሁ ጠብቁ አልኋቸው።
30፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አምላካችን ቤት ይወስዱት ዘንድ ብሩንና ወርቁን ዕቃዎቹንም በሚዛን ተቀበሉ።
31፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም እንሄድ ዘንድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን የአምላካችንም እጅ በላያችን ነበረ፥ በመንገድም ከጠላትና ከሚሸምቅ ሰው እጅ አዳነን።
32፤ ወደ ኢየሩሳሌም ደረስን፥ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥን።
33፤ በአራተኛውም ቀን ብሩና ወርቁ ዕቃዎቹም በአምላካችን ቤት በካህኑ በኦርዮ ልጅ በሜሪሞት እጅ ተመዘኑ፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር ነበረ ከእነርሱም ጋር ሌዋውያን የኢያሱ ልጅ ዮዛባትና የቢንዊ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ።
34፤ ሁሉም በቍጥርና በሚዛን ተመዘነ፤ ሚዛኑም ሁሉ በዚያን ጊዜ ተጻፈ።
35፤ ከምርኮም የወጡት ምርኮኞች ለእስራኤል አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት ስለ እስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ዘጠና ስድስትም አውራ በጎች፥ ሰባ ሰባትም ጠቦቶች፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ።
36፤ የንጉሡንም ትእዛዝ በወንዙ ማዶ ላሉት ለንጉሡ ሹማምቶችና ገዦች ሰጡ፤ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት አገዙ።