መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ። 8

1፤ ኤልሳዕም ልጅዋን ያስነሣላትን ሴት። አንቺ ከቤተ ሰብሽ ጋር ተነሥተሽ ሂጂ፥ በምታገኚውም ስፍራ ተቀመጪ፤ እግዚአብሔር ራብ ጠርቶአል፤ ሰባት ዓመትም በምድር ላይ ይመጣል ብሎ ተናገራት።

2፤ ሴቲቱም ተነሥታ እንደ እግዚአብሔር ሰው ቃል አደረገች፤ ከቤተ ሰብዋም ጋር ሄዳ በፍልስጥኤም አገር ሰባት ዓመት ተቀመጠች።

3፤ ሰባቱም ዓመት በተፈጸመ ጊዜ ሴቲቱ ከፍልስጥኤም አገር ተመለሰች፤ ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ልትጮኽ ወደ ንጉሡ ወጣች።

4፤ ንጉሡም ከእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ከግያዝ ጋር። ኤልሳዕ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ ንገረኝ እያለ ይጫወት ነበር።

5፤ እርሱም የሞተውን እንደ አስነሣ ለንጉሡ ሲናገር፥ እነሆ፥ ልጅዋን ያስነሣላት ሴት ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ወደ ንጉሥ ጮኸች፤ ግያዝም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ሴቲቱ ይህች ናት፥ ኤልሳዕም ያስነሣው ልጅዋ ይህ ነው አለ።

6፤ ንጉሡም ሴቲቱን ጠየቀ፥ ነገረችውም። ንጉሡም። የነበረላትን ሁሉ፥ መሬትዋንም ከተወች ጀምራ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን የእርሻዋን ፍሬ ሁሉ መልስላት ብሎ ስለ እርስዋ ጃንደረባውን አዘዘ።

7፤ ኤልሳዕም ወደ ደማስቆ መጣ፤ የሶርያም ንጉሥ ወልደ አዴር ታምሞ ነበር፤ ወሬኞችም። የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቶአል ብለው ነገሩት።

8፤ ንጉሡም አዛሄልን። ገጸ በረከት በእጅህ ወስደህ የእግዚአብሔርን ሰው ልትገናኝ ሂድ፤ በእርሱም አፍ። ከዚህ በሽታ እድናለሁን? ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ አለው።

9፤ አዛሄልም ሊገናኘው ሄደ፥ ከእርሱም ጋር ከደማስቆ መልካሙን ነገር ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ወሰደ፤ መጥቶም በፊቱ ቆመና። ልጅህ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር። ከዚህ በሽታ እድናለሁን? ሲል ወደ አንተ ልኮኛል አለ።

10፤ ኤልሳዕም። ሂድ፥ መዳንስ ትድናለህ በለው፤ ነገር ግን እንዲሞት እግዚአብሔር አሳይቶኛል አለው።

11፤ እስኪያፍርም ድረስ ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ የእግዚአብሔርም ሰው አነባ።

12፤ አዛሄልም። ጌታዬ ለምን ያነባል? አለ። እርሱም። በእስራኤል ልጆች ላይ የምታደርገውን ክፋት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፥ ጕልማሶቻቸውንም በሰይፍ ትገድላለህ፥ ሕፃናቶቻቸውንም ትፈጠፍጣለህ፥ እርጉዞቻቸውንም ትቀድዳለህ አለው።

13፤ አዛሄልም። ይህን ታላቅ ነገር አደርግ ዘንድ እኔ ውሻ ባሪያህ ምንድር ነኝ? አለ። ኤልሳዕም። አንተ በሶርያ ላይ ንጉሥ እንድትሆን እግዚአብሔር አሳይቶኛል አለው።

14፤ ከኤልሳዕም ርቆ ወደ ጌታው መጣ፤ እርሱም። ኤልሳዕ ምን አለህ? አለው።

15፤ እርሱም። እንድትፈወስ ነገረኝ አለው። በነጋውም ለሐፍ ወስዶ በውኃ ነከረው በፊቱም ላይ ሸፈነው፥ ሞተም። አዛሄልም በፋንታው ነገሠ።

16፤ በእስራኤልም ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በአምስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም ነገሠ።

17፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ።

18፤ የአክዓብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ።

19፤ ነገር ግን ለእርሱና ለልጆቹ ለዘመኑ ሁሉ መብራት ይሰጠው ዘንድ ተስፋ እንደ ሰጠ፥ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት እግዚአብሔር ይሁዳን ያጠፋ ዘንድ አልወደደም።

20፤ በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ ለይሁዳ እንዳይገብር ሸፈተ፥ በላያቸውም ንጉሥ አነገሡ።

21፤ ኢዮራምም ከሰረገሎቹ ሁሉ ጋር ወደ ጸዒር አለፈ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሰረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ፤ ሕዝቡ ግን ወደ ድንኳኑ ሸሸ።

22፤ ኤዶምያስ ግን ለይሁዳ እንዳይገብር እስከ ዛሬ ድረስ ሸፈተ። በዚያም ዘመን ደግሞ ልብና ሸፈተ።

23፤ የተረፈውም የኢዮራም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

24፤ ኢዮራምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በፋንታውም ልጁ አካዝያስ ነገሠ።

25፤ በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በአሥራ ሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ።

26፤ መንገሥ በጀመረ ጊዜ አካዝያስ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የእስራኤል ንጉሥ የዘንበሪ ልጅ ነበረች።

27፤ በአክዓብም ቤት መንገድ ሄደ፥ እንደ አክዓብም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ለአክዓብ ቤት አማች ነበረና።

28፤ ከአክዓብም ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገለዓድ ሊጋጠም ሄደ፤ ሶርያውንም ኢዮራምን አቆሰሉት።

29፤ ንጉሡም ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ። የአክዓብም ልጅ ኢዮራም ታምሞ ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ሊያየው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።