መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ። 11

1፤ የአካዝያስም እናት ጎቶልያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የመንግሥትን ዘር ሁሉ አጠፋች።

2፤ የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ወስዳ ከተገደሉት ከንጉሥ ልጆች መካከል ሰረቀችው፤ እርሱንና ሞግዚቱንም ወደ እልፍኝ ወሰደች፥ እንዳይገደልም ከጎቶልያ ሸሸጉት።

3፤ በእርስዋም ዘንድ ተሸሸጎ በእግዚአብሔር ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። ጎቶልያም በምድር ላይ ነገሠች።

4፤ በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ በካራውያንና በዘበኞች ላይ ያሉትን የመቶ አለቆች ወሰደ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት አገባቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አማላቸው፥ የንጉሡንም ልጅ አሳያቸው።

5፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። እንዲህ አድርጉ፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ የንጉሡን ቤት ዘብ ጠብቁ፤

6፤ ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ በሱር በር ሁኑ፤ አንዱም እጅ ከዘበኞች ቤት በኋላ ባለው በር ሁኑ፤ ቤቱንም ጠብቁ፥ ከልክሉም፤

7፤ ከእናንተም በሰንበት ቀን የምትወጡት ሁለቱ እጅ በንጉሥ ዙሪያ ሆናችሁ የእግዚአብሔርን ቤት ጠብቁ።

8፤ ንጉሡንም በዙሪያው ክበቡት፥ የጦር ዕቃችሁም በእጃችሁ ይሁን፤ በሰልፋችሁ መካከል የሚገባ ይገደል፤ ንጉሡም በወጣና በገባ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁኑ።

9፤ መቶ አለቆችም ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ በሰንበት ይገቡ የነበሩትን፥ በሰንበቱም ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ።

10፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር ሁሉ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው።

11፤ ዘበኞቹም ሁሉ እያንዳንዳቸው የጦር ዕቃቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ ቆሙ።

12፤ የንጉሡንም ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነበት፥ ምስክሩንም ሰጠው፤ ቀብተውም ንጉሥ አደረጉትና። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ እያሉ እጃቸውን አጨበጨቡ።

13፤ ጎቶልያም የሠራዊቱንና የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች።

14፤ እነሆም፥ ንጉሡ እንደ ተለመደው በዓምዱ አጠገብ ቆሞ፥ ከንጉሡም ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች፤ የአገሩም ሕዝብ ሁል ደስ ብሎአቸው ቀንደ መለከት ይነፉ ነበር። ጎቶልያም ልብስዋን ቀድዳ። ዓመፅ ነው፥ ዓመፅ ነው ብላ ጮኸች።

15፤ ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች። ወደ ሰልፉ መካከል አውጡአት፤ የሚከተላትንም በሰይፍ ግደሉት ብሎ አዘዛቸው፤ ካህኑ። በእግዚአብሔር ቤት አትገደል ብሎአልና።

16፤ እጃቸውንም በእርስዋ ላይ ጫኑ፥ በፈረሱም መግቢያ መንገድ ወደ ንጉሥ ቤት ወሰዱአት፥ በዚያም ገደሉአት።

17፤ ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን አደረገ፤ ደግሞም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን አደረገ።

18፤ የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በኣል ቤት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን አደቀቁ፥ የበኣልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። ካህኑም ለእግዚአብሔር ቤት አስተዳዳሪዎችን ሾመ።

19፤ መቶ አለቆቹንና ካራውያንንም፥ ዘበኞችንና የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፤ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረዱት፥ በዘበኞችም በር መንገድ ወደ ንጉሡ ቤት አመጡት፤ በነገሥታቱም ዙፋን ተቀመጠ።

20፤ የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች። ጎቶልያንም በንጉሡ ቤት አጠገብ በሰይፍ ገደሉአት።

21፤