መጽሐፈ ሳሙኤል ካል 16
1፤ ዳዊትም ከተራራው ራስ ጥቂት ፈቀቅ ባለ ጊዜ የሜምፊቦስቴ ባሪያ ሲባ ሁለት መቶ እንጀራ፥ አንድ መቶም ዘለላ ዘቢብ፥ አንድ መቶም በለስ፥ አንድ አቁማዳም ወይን ጠጅ የተጫኑ ሁለት አህዮች እየነዳ ተገናኘው።
2፤ ንጉሡም ሲባን። ይህ ምንድር ነው? አለው። ሲባም። አህዮቹ የንጉሥ ቤተ ሰቦች ይቀመጡባቸው ዘንድ፥ እንጀራውና በለሱ ብላቴኖቹ ይበሉት ዘንድ፥ የወይን ጠጁም በበረሀ የሚደክሙት ይጠጡት ዘንድ ነው አለ።
3፤ ንጉሡም። የጌታህ ልጅ ወዴት ነው? አለ። ሲባም ንጉሡን። እነሆ። የእስራኤል ቤት ዛሬ የአባቴን መንግሥት ይመልስልኛል ብሎ በኢየሩሳሌም ተቀምጦአል አለው።
4፤ ንጉሡም ሲባን። እነሆ፥ ለሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ለአንተ ይሁን አለው። ሲባም። እጅ እነሣለሁ፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በፊትህ ሞገስ ላግኝ አለ።
5፤ ንጉሡ ዳዊትም ወደ ብራቂም መጣ፤ እነሆም፥ ሳሚ የሚባል የጌራ ልጅ ከሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ከዚያ ወጣ፥ እየሄደም ይረግመው ነበር።
6፤ ወደ ዳዊትና ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ባሪያዎችም ድንጋይ ይወረውር ነበር፤ በንጉሡም ቀኝና ግራ ሕዝቡ ሁሉና ኃያላኑ ሁሉ ነበሩ።
7፤ ሳሚም ሲረግም። ሂድ፥ አንተ የደም ሰው፥ ምናምንቴ፥ ሂድ።
8፤ በፋንታው ነግሠሃልና እግዚአብሔር የሳኦልን ቤት ደም ሁሉ መለሰብህ፤ እግዚአብሔርም መንግሥትን ለልጅህ ለአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ እነሆም፥ አንተ የደም ሰው ነህና በመከራ ተይዘሃል አለ።
9፤ የጽሩያም ልጅ አቢሳ ንጉሡን። ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን ስለምን ይረግማል? ልሂድና ራሱን ልቍረጠው አለው።
10፤ ንጉሡም። እናንተ የጽሩም ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር። ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ፤ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? አለ።
11፤ ዳዊትም አቢሳንና ባሪያዎቹን ሁሉ። እነሆ ከወገቤ የወጣው ልጄ ነፍሴን ይሻል፤ ይልቁንስ ይህ የብንያም ልጅ እንዴት ነዋ? እግዚአብሔር አዝዞታልና ተዉት፥ ይርገመኝ።
12፤ ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል አላቸው።
13፤ ዳዊትና ሰዎቹም በመንገድ ይሄዱ ነበር፤ ሳሚም በተራራው አጠገብ በእርሱ ትይዩ እየሄደ ይራገም፤ ድንጋይም ይወረውር፥ ትቢያም ይበትን ነበር።
14፤ ንጉሡና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ሁሉ ደክመው ነበር፥ በዚያም ዐረፉ።
15፤ አቤሴሎምና ሕዝቡ ሁሉ የእስራኤልም ሰዎች አኪጦፌልም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
16፤ የዳዊትም ወዳጅ አርካዊው ኩሲ ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ ኩሲ። ሺህ ዓመት ያንግሥህ አለው።
17፤ አቤሴሎምም ኩሲን። ስለ ወዳጅህ ያደረግኸው ቸርነት ይህ ነውን? ከወዳጅህ ጋር ያልሄድህ ስለምንድር ነው? አለው።
18፤ ኩሲም አቤሴሎምን። እንዲህ አይደለም፤ ከእግዚአብሔር ከዚህም ሕዝብ ከእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ለተመረጠው ለእርሱ እሆናለሁ ከእርሱም ጋር እቀመጣለሁ።
19፤ ዳግምም የማገለግል ለማን ነው? በንጉሥ ልጅ ፊት አይደለምን? በአባትህ ፊት እንዳገለገልሁ እንዲሁ በአንተ ፊት እሆናለሁ አለው።
20፤ አቤሴሎምም አኪጦፌልን። ምከሩ ምን እናድርግ? አለው።
21፤ አኪጦፌልም አቤሴሎምን። ቤት ሊጠብቁ ወደ ተዋቸው ወደ አባትህ ቁባቶች ግባ፤ እስራኤልም ሁሉ አባትህን እንዳሳፈርኸው ይሰማሉ፤ ከአንተም ጋር ያሉት ሁሉ እጃቸው ይበረታል አለው።
22፤ ለአቤሴሎምም በሰገነት ላይ ድንኳን ተከሉለት፤ አቤሴሎምም በእስራኤል ሁሉ ፊት ወደ አባቱ ቁባቶች ገባ።
23፤ በዚያም ወራት የመከራት የአኪጦፌል ምክር የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ነበረች፤ የአኪጦፌልም ምክር ሁሉ ከዳዊትና ከአቤሴሎም ጋር እንዲህ ነበረች።