መጽሐፈ ሳሙኤል ካል 11
1፤ እንዲህም ሆነ፤ በዓመቱ መለወጫ ነገሥታት ወደ ሰልፍ በሚወጡበት ጊዜ፥ ዳዊት ኢዮአብን ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹን እስራኤልንም ሁሉ ሰደደ። የአሞንም ልጆች አገር አጠፉ፥ ረባትንም ከበቡ፤ ዳዊት ግን በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር።
2፤ እንዲህም ሆነ፤ ወደ ማታ ጊዜ ዳዊት ከምንጣፉ ተነሣ፥ በንጉሥም ቤት በሰገነት ላይ ተመላለሰ፤ በሰገነቱ ሳለ አንዲት ሴት ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም መልከ መልካም ነበረች።
3፤ ዳዊትም ልኮ ስለ ሴቲቱ ጠየቀ፤ አንድ ሰውም። ይህች የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን? አለ።
4፤ ዳዊትም መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ ወደ እርሱም ገባች፥ ከርኵሰትዋም ነጽታ ነበርና ከእርስዋ ጋር ተኛ፤ ወደ ቤትዋም ተመለሰች።
5፤ ሴቲቱም አረገዘች፥ ወደ ዳዊትም። አርግዤአለሁ ብላ ላከችበት።
6፤ ዳዊትም ወደ ኢዮአብ። ኬጢያዊውን ኦርዮን ስደድልኝ ብሎ ላከ። ኢዮአብም ኦርዮን ወደ ዳዊት ሰደደው።
7፤ ኦርዮም ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ዳዊት የኢዮአብንና የሕዝቡን ደኅንነት፥ ሰልፉም እንዴት እንደ ሆነ ጠየቀው።
8፤ ዳዊትም ኦርዮን። ወደ ቤትህ ሂድ፥ እግርህንም ታጠብ አለው። ኦርዮም ከንጉሡ ቤት ሲወጣ ማለፊያ የንጉሥ መብል ተከትሎት ሄደ።
9፤ ኦርዮ ግን ከጌታው ባሪያዎች ሁሉ ጋር በንጉሥ ቤት ደጅ ተኛ፥ ወደ ቤቱም አልወረደም።
10፤ ኦርዮ ወደ ቤቱ አልሄደም ብለው ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም ኦርዮን። አንተ ከመንገድ የመጣህ አይደለምን? ስለ ምን ወደ ቤትህ አልወረድህም? አለው።
11፤ ኦርዮም ዳዊትን። ታቦቱና እስራኤል ይሁዳም በጎጆ ተቀምጠዋል፤ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ባሪያዎች በሰፊ ሜዳ ሰፍረዋል፤ እኔ ልበላና ልጠጣ ወይስ ከሚስቴ ጋር ልተኛ ወደ ቤቴ እሄዳለሁን? በሕይወትህና በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ይህን ነገር አላደርገውም አለው።
12፤ ዳዊትም ኦርዮን። ዛሬ ደግሞ በዚህ ተቀመጥ፥ ነገም አሰናብትሃለሁ አለው። ኦርዮም በዚያ ቀንና በነጋው በኢየሩሳሌም ተቀመጠ።
13፤ ዳዊትም ጠራው፥ በፊቱም በላና ጠጣ፥ አሰከረውም፤ ነገር ግን በመሸ ጊዜ ወጥቶ ከጌታው ባሪያዎች ጋር በምንጣፉ ላይ ተኛ፥ ወደ ቤቱም አልወረደም።
14፤ በነጋም ጊዜ ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጻፈ፥ በኦርዮም እጅ ላከው።
15፤ በደብዳቤውም። ኦርዮን ጽኑ ሰልፍ ባለበት በፊተኛው ስፍራ አቁሙት፥ ተመትቶም ይሞት ዘንድ ከኋላው ሽሹ ብሎ ጻፈ።
16፤ ኢዮአብም ከተማይቱን በከበበ ጊዜ ጀግኖች እንዳሉበት በሚያውቀው ስፍራ ኦርዮን አቆመው።
17፤ የከተማይቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ተዋጉ፤ ከዳዊትም ባሪያዎች ከሕዝቡ አንዳንዱ ወደቁ፤ ኬጢያዊው ኦርዮም ደግሞ ሞተ።
18፤ ኢዮአብም ልኮ በሰልፍ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ነገረው።
19፤ ለመልእክተኛውም እንዲህ ብሎ አዘዘው። የሰልፉን ነገር ሁሉ ለንጉሡ ነግረህ በፈጸምህ ጊዜ።
20፤ ስትዋጉ ወደ ከተማይቱ ለምን ቀረባችሁ? ከቅጥሩ በላይ ፍላጻ እንዲወረወር አታውቁምን?
21፤ የሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን ማን ገደለው? ከቅጥር ላይ የወፍጮ መጅ ጥላ በቴቤስ ላይ የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ስለ ምን ወደ ቅጥሩ እንደዚህ ቀርባችሁ? ብሎ ንጉሡ ሲቈጣ ብታይ፥ አንተ። ባሪያህ ኬጢያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ በለው።
22፤ መልእክተኛውም ተነሥቶ ሄደ፥ ኢዮአብም ያዘዘውን ሁሉ ለዳዊት ነገረው።
23፤ መልእክተኛውም ዳዊትን። ሰዎቹ በረቱብን፥ ወደ ሜዳም ወጡብን፤ እኛም ወደቅንባቸው፥ እስከ ከተማይቱም በር ድረስ ተከተልናቸው።
24፤ ፍላጻ የሚወረውሩም በቅጥሩ ላይ ሆነው በባሪያዎችህ ላይ ወረወሩ፤ ከንጉሡም ባሪያዎች አንዳንድ ሞቱ፥ ባሪያህም ኬጢያዊው ኦርዮ ደግሞ ሞተ አለው።
25፤ ዳዊትም መልእክተኛውን። ሰይፍ አንድ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜም ያን ያጠፋልና ይህ ነገር በዓይንህ አይክፋ፤ ከተማይቱን የሚወጉትን አበርታ፥ አፍርሳትም ብለህ ለኢዮአብ ንገረው፤ አንተም አጽናው አለው።
26፤ የኦርዮም ሚስት ባልዋ ኦርዮ እንደሞተ በሰማች ጊዜ ለባልዋ አለቀሰች።
27፤ የልቅሶዋም ወራት ሲፈጸም ዳዊት ልኮ ወደ ቤቱ አስመጣት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወንድ ልጅም ወለደችለት፤ ነገር ግን ዳዊት ያደረገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ።