መጽሐፈ መሣፍንት 16
1፤ ሶምሶንም ወደ ጋዛ ሄደ፥ በዚያም ጋለሞታ ሴት አይቶ ወደ እርስዋ ገባ።
2፤ የጋዛ ሰዎችም ሶምሶን ወደ ከተማ ውስጥ እንደ ገባ ሰሙ፥ ከበቡትም፥ ሌሊቱንም ሁሉ በከተማይቱ በር ሸመቁበት። ማለዳ እንገድለዋለን ብለውም ሌሊቱን ሁሉ በዝምታ ተቀመጡ።
3፤ ሶምሶንም እስከ እኩለ ሌሊት ተኛ፤ እኩለ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ተነሥቶ የከተማይቱን በር መዝጊያ ያዘ፥ ከሁለቱ መቃኖችና ከመወርወሪያውም ጋር ነቀለው፥ በትከሻውም ላይ አደረገ፥ በኬብሮንም ፊት ወዳለው ተራራ ራስ ላይ ተሸክሞት ወጣ በዚያም ጣለው።
4፤ ከዚህም በኋላ በሶሬቅ ሸለቆ የነበረች ደሊላ የተባለች አንዲት ሴትን ወደደ።
5፤ የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ወደ እርስዋ ወጥተው። እርሱን ሸንግለሽ በእርሱ ያለ ታላቅ ኃይል በምን እንደ ሆነ፥ እኛስ እርሱን ለማዋረድ እናስረው ዘንድ የምናሸንፈው በምን እንደ ሆነ እወቂ፤ እኛም እያንዳንዳችን ሺህ አንድ መቶ ብር ሺህ አንድ መቶ ብር እንሰጥሻለን አሉአት።
6፤ ደሊላም ሶምሶንን። ታላቅ ኃይልህ በምን እንደ ሆነ፥ እንድትዋረድስ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለችው።
7፤ ሶምሶንም። በሰባት ባልደረቀ በእርጥብ ጠፍር ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት።
8፤ የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ሰባት ያልደረቀ እርጥብ ጠፍር አመጡላት፥ በእርሱም አሰረችው።
9፤ በጓዳዋም ውስጥ ሰዎች ተደብቀው ነበር። እርስዋም። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። እርሱም የተልባ እግር ፈትል እሳት በሸተተው ጊዜ እንዲበጠስ ጠፍሩን በጣጠሰው፤ ኃይሉም በምን እንደ ሆነ አልታወቀም።
10፤ ደሊላም ሶምሶንን። እነሆ፥ አታለልኸኝ፥ የነገርኸኝም ሀሰት ነው፤ አሁንም የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለችው።
11፤ እርሱም። ሥራ ባልተሠራበት በአዲስ ገመድ ቢያስሩኝ፥ እደክማለሁ፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት።
12፤ ደሊላም አዲስ ገመድ ወስዳ በእርሱ አሰረችው፤ በጓዳዋም የተደበቁ ሰዎች ተቀምጠው ነበር። እርስዋም። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ገመዱንም ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሰው።
13፤ ደሊላም ሶምሶንን። እስከ አሁን ድረስ አታለልኸኝ፥ የነገርኸኝም ሐሰት ነው፤ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ ንገረኝ አለችው። እርሱም። የራሴን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድር ጋር ብትጐነጕኚው፥ በችካልም ብትቸክዪው፥ እደክማለሁ፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ አላት።
14፤ ሶምሶንም በተኛ ጊዜ ደሊላ የራሱን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድሩ ጋር ጐነጐነችው፥ በችካልም ቸከለችውና። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቃ፥ ችካሉንም ከነቆንዳላው ድሩንም ነቀለ።
15፤ እርስዋም። አንተ። እወድድሻለሁ እንዴት ትለኛለህ፥ ልብህ ከእኔ ጋር አይደለም? ስታታልለኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው፥ ታላቅ ኃይልህም በምን እንደ ሆነ አልነገርኸኝም አለችው።
16፤ ዕለት ዕለትም በቃልዋ ነዘነዘችው አስቸገረችውም፥ ነፍሱም እስከ ሞት ድረስ ተጨነቀች።
17፤ እርሱም። ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ ለእግዚአብሔር የተለየሁ ነኝና በራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም፤ የራሴንም ጠጕር ብላጭ ኃይሌ ከእኔ ይሄዳል፥ እደክማለሁም፥ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ ብሎ የልቡን ሁሉ ገለጠላት።
18፤ ደሊላም የልቡን ሁሉ እንደ ገለጠላት ባየች ጊዜ። የልቡን ሁሉ ገልጦልኛልና ይህን ጊዜ ደግሞ ኑ ብላ ላከችና የፍልስጥኤማውያንን መኳንንት ጠራች። የፍልስጥኤማውያን መኳንንትም ብሩን በእጃቸው ይዘው ወደ እርስዋ መጡ።
19፤ እርስዋም በጕልበትዋ ላይ አስተኛችው፤ አንድ ሰውም ጠራች፥ እርሱም ሰባቱን የራሱን ጕንጕን ላጨው። ልታዋርደውም ጀመረች፥ ኃይሉም ከእርሱ ሄደ።
20፤ እርስዋም። ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቅቶ። እወጣለሁ እንደ ወትሮውም ጊዜ አደርጋለሁ አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደ ተለየው አላወቀም።
21፤ ፍልስጥኤማውያንም ይዘው ዓይኖቹን አወጡት፤ ወደ ጋዛም አምጥተው በናስ ሰንሰለት አሰሩት፤ በግዞትም ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር።
22፤ የራሱም ጠጕር ከላጩት በኋላ ያድግ ጀመር።
23፤ የፍልስጥኤምም መኳንንት። አምላካችን ጠላታችንን ሶምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን እያሉ ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ ደስም ይላቸው ዘንድ ተሰበሰቡ።
24፤ ሕዝቡም ሁሉ ባዩት ጊዜ። ምድራችንን ያጠፋውን፥ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ።
25፤ ልባቸውንም ደስ ባለው ጊዜ። በፊታችን እንዲጫወት ሶምሶንን ጥሩት አሉ። ሶምሶንንም ከግዞት ቤት ጠሩት፥ በፊታቸውም ተጫወተ፤ ተዘባበቱበትም፥ በምሰሶና በምሰሶም መካከል አቆሙት።
26፤ ሶምሶንም እጁን የያዘውን ብላቴና። ቤቱን የደገፉትን ምሰሶች እጠጋባቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ አስይዘኝ አለው።
27፤ በቤትም ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ሞልተውበት ነበር፥ የፍልስጥኤምም መኳንንት ሁሉ በዚያ ነበሩ፤ በቤቱም ሰገነት ላይ ሶምሶን ሲጫወት የሚያዩ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ።
28፤ ሶምሶንም። ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እባክህ፥ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፥ እባክህ፥ አበርታኝ ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ።
29፤ ሶምሶንም ቤቱ ተደግፎባቸው የነበሩትን ሁለቱን መካከለኞች ምሰሶች ያዘ፤ አንዱን በቀኝ እጁ አንዱንም በግራ እጁ ይዞ ተጠጋባቸው።
30፤ ሶምሶንም። ከፍልስጥኤማውያን ጋር ልሙት አለ፤ ተጎንብሶም ምሰሶቹን በሙሉ ኅይሉ ገፋ፥ ቤቱም በውስጡ በነበሩት በመኳንንቱም በሕዝቡም ሁሉ ላይ ወደቀ፤ በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ።
31፤ ወንድሞቹም የአባቱ ቤተ ሰቦችም ሁሉ ወረዱ፥ ይዘውም አመጡት፤ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ቀበሩት። እርሱም በእስራኤል ላይ ሀያ ዓመት ፈረደ። a