የዮሐንስ ራእይ 10
1 ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፥
2 የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፥ እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።
3 በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ።
4 ሰባቱ ነጐድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፤ ከሰማይም። ሰባቱ ነጐድጓድ የተናገሩትን ነገር በማኅተም ዝጋው አትጻፈውም የሚል ድምፅ ሰማሁ።
5 በባሕርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አሻቅቦ ዘረጋ፥
6 ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፥ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፥ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፥ ከዘላለምም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ።
7 ወደ ፊት አይዘገይም፥ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን፥ ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል አለ።
8 ከሰማይም የሰማሁት ድምፅ እንደ ገና ሲናገረኝና። ሂድና በባሕርና በምድር ላይ ከሚቆመው መልአክ በእጁ ያለችውን የተከፈተችውን መጽሐፍ ውሰድ ሲል ሰማሁ።
9 ወደ መልአኩም ሄጄ። ታናሺቱን መጽሐፍ ስጠኝ አልሁት። እርሱም። ውሰድና ብላት፥ ሆድህንም መራራ ታደርገዋለች በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች አለኝ።
10 ከመልአኩም እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፤ ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ።
11 በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ እንደ ገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል ተባለልኝ።