የማርቆስ ወንጌል 8
1 በዚያ ወራት ደግሞ ብዙ ሕዝብ ነበረ የሚበሉትም ስለሌላቸው ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ።
2 ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤
3 ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ አላቸው።
4 ደቀ መዛሙርቱም። በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት።
5 እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው፥ እነርሱም። ሰባት አሉት።
6 ሕዝቡም በምድር እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፥ ቈርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ለሕዝቡም አቀረቡ።
7 ጥቂትም ትንሽ ዓሣ ነበራቸው፤ ባረከውም ይህንም ደግሞ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ።
8 በሉም ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ።
9 የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ።
10 አሰናበታቸውም። ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ።
11 ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር።
12 በመንፈሱም እጅግ ቃተተና። ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ።
13 ትቶአቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ማዶ ሄደ።
14 እንጀራ መያዝም ረሱ፥ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም።
15 እርሱም። ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው።
16 እርስ በርሳቸውም። እንጀራ ስለሌለን ይሆናል ብለው ተነጋገሩ።
17 ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን?
18 ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዓይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን?
19 አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እነርሱም። አሥራ ሁለት አሉት።
20 ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም። ሰባት አሉት።
21 ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው።
22 ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት።
23 ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፥ በዓይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት። አንዳች ታያለህን ብሎ ጠየቀው።
24 አሻቅቦም። ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ አለ።
25 ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዓይኑ ላይ ጫነበት አጥርቶም አየና ዳነም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ።
26 ወደ ቤቱም ሰደደውና። ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው።
27 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም። ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው።
28 እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት።
29 እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም። አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት።
30 ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።
31 የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር።
32 ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።
33 እርሱ ግን ዘወር አለ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና አለው።
34 ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።
35 ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል።
36 ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?
37 ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?
38 በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።