ትንቢተ ዮናስ 2

1፤ እግዚአብሔርም ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ዮናስም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በዓሣው ሆድ ውስጥ ነበረ።

2፤ ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እንዲህም አለ።

3፤ በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እርሱም ሰማኝ፤ በሲኦልም ሆድ ውስጥ ሆኜ ጮኽሁ፥ ቃሌንም አዳመጥህ።

4፤ ወደ ጥልቁ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣልኸኝ፥ ፈሳሾችም በዙሪያዬ ነበሩ፤ ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፉ።

5፤ እኔም። ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፤ ነገር ግን ወደ ቅዱስ መቅደስህ ደግሞ እመለከታለሁ አልሁ።

6፤ ውኆችም እስከ ነፍሴ ድረስ ከበቡኝ፤ ጥልቁ ባሕር በዙሪያዬ ነበረ፤ የባሕሩ ሣር በራሴ ተጠምጥሞ ነበር።

7፤ ወደ ተራሮች መሠረት ወረድሁ፤ በምድርና በመወርወሪያዎችዋ ለዘላለም ተዘጋሁ፤ አንተ ግን፥ አቤቱ አምላኬ፥ ሕይወቴን ከጕድጓዱ አወጣህ።

8፤ ነፍሴ በዛለችብኝ ጊዜ እግዚአብሔርን አሰብሁት፤ ጸሎቴም ወደ አንተ ወደ ቅዱስ መቅደስህ ገባች።

9፤ ከንቱነትንና ሐሰትን የሚጠብቁ ምሕረታቸውን ትተዋል።

10፤ እኔ ግን በምስጋና ቃል እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እከፍላለሁ። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

[11]፤ እግዚአብሔርም ዓሣውን አዘዘው፥ እርሱም ዮናስን በየብስ ላይ ተፋው።