ትንቢተ ዳንኤል 11
1፤ እኔም በሜዶናዊ በዳርዮስ መጀመሪያ ዓመት አጸናውና አበረታው ዘንድ ቆሜ ነበር።
2፤ አሁንም እውነትን አሳይሃለሁ። እነሆ፥ ሦስት ነገሥታት ደግሞ በፋርስ ይነሣሉ፤ አራተኛውም ከሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጠጋ ይሆናል፤ በባለጠግነቱም በበረታ ጊዜ በግሪክ መንግሥት ላይ ሁሉን ያስነሣል።
3፤ ኃያልም ንጉሥ ይነሣል፥ በትልቅ አገዛዝም ይገዛል፥ እንደ ፈቃዱም ያደርጋል።
4፤ እርሱም በተነሣ ጊዜ መንግሥቱ ይሰበራል፤ እስከ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ይከፋፈላል። ለዘሩ ግን አይከፋፈልም፥ እንደ ገዛበትም አገዛዝ አይሆንም፤ መንግሥቱ ይነቀላልና፤ ከእነዚህም ለሌሎች ይሆናልና።
5፤ የደቡብም ንጉሥ ከአለቆቹም አንዱ ይበረታሉ፤ እርሱም ይበረታበታል ይሠለጥንማል፤ ግዛቱም ታላቅ ግዛት ይሆናል።
6፤ ከዘመናትም በኋላ ይጋጠማሉ፤ የደቡብም ንጉሥ ሴት ልጅ ቃል ኪዳን ለማድረግ ወደ ሰሜን ንጉሥ ትመጣለች፤ የክንድዋ ኃይል ግን አይጸናም፥ እርሱና ክንዱም አይጸናም፤ እርስዋና እርስዋን ያመጡ የወለዳትም በዚያም ዘመን ያጸናት አልፈው ይሰጣሉ።
7፤ ነገር ግን ከሥርዋ ቍጥቋጥ አንዱ በስፍራው ይነሣል፤ ወደ ሠራዊቱም ይመጣል፥ ወደ ሰሜንም ንጉሥ አምባ ይገባል፥ በላያቸውም ያደርጋል፥ ያሸንፍማል።
8፤ አማልክቶቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎቻቸውን ከብርና ከወርቅም የተሠሩትን የከበሩትን ዕቃዎች ወደ ግብጽ ይማርካል፤ እስከ ጥቂትም ዓመት ድረስ ከሰሜን ንጉሥ ጋር ሳይዋጋ ይቀመጣል።
9፤ ይህም ወደ ደቡብ ንጉሥ መንግሥት ይገባል፥ ነገር ግን ወደ ገዛ ምድሩ ይመለሳል።
10፤ ልጆቹም ይዋጋሉ፤ ብዙ ሠራዊትንና ሕዝብን ይሰበስባል፤ እርሱም ይመጣል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል፤ ተመልሶም እስከ አምባው ድረስ ይዋጋል።
11፤ የደቡብም ንጉሥ ይቈጣል ወጥቶም ከሰሜን ንጉሥ ጋር ይዋጋል፤ ብዙ ሕዝብንም ለሰልፍ ያቆማል፥ ሕዝቡም አልፎ በእጁ ይሰጣል።
12፤ ሕዝቡም በተወሰደ ጊዜ ልቡ ይታበያል፤ አእላፋትንም ይጥላል፥ ነገር ግን አያሸንፍም።
13፤ የሰሜንም ንጉሥ ይመለሳል፥ ከቀደመውም የበለጠ ብዙ ሕዝብ ለሰልፍ ያቆማል፤ በዘመናትና በዓመታትም ፍጻሜ ከታላቅ ሠራዊትና ከብዙ ሀብት ጋር ይመጣል።
14፤ በዚያም ዘመን ብዙ ሰዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፤ ከሕዝብህም መካከል የዓመፅ ልጆች ራእዩን ያጸኑ ዘንድ ይነሣሉ፤ ነገር ግን ይወድቃሉ።
15፤ የሰሜንም ንጉሥ ይመጣል፥ አፈርንም ይደለድላል፥ የተመሸገችንም ከተማ ይወስዳል፤ የደቡብም ሠራዊት የተመረጡትም ሕዝቡ አይቆሙም፤ ለመቋቋምም ኃይል የላቸውም።
16፤ በእርሱም ላይ የሚመጣው ግን እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፥ በፊቱም የሚቆም የለም፤ በመልካሚቱም ምድር ይቆማል፥ በእጁም ውስጥ ጥፋት ይሆናል።
17፤ ከመንግሥቱም ሁሉ ኃይል ጋር ይመጣ ዘንድ ፊቱን ያቀናል፥ ከእርሱም ጋር አንድነትን ያደርጋል፤ ያረክሳትም ዘንድ ሴትን ልጅ ይሰጠዋል፤ እርስዋም አትጸናም ለእርሱም አትሆንም።
18፤ ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ደሴቶች ይመልሳል፥ ብዙዎችንም ይወስዳል፤ አንድ አለቃ ግን ስድቡን ይሽራል፥ ስድቡንም በራሱ ላይ ይመልሳል።
19፤ ፊቱንም ወደ ገዛ ምድሩ አምባዎች ይመልሳል፤ ተሰናክሎም ይወድቃል፥ አይገኝምም።
20፤ የዚያን ጊዜም በመንግሥቱ ክብር መካከል አስገባሪውን የሚያሳልፍ በስፍራው ይነሣል፤ ነገር ግን በቍጣው ሳይሆን በሰልፍም ሳይሆን በጥቂት ቀን ይሰበራል።
21፤ በእርሱም ስፍራ የተጠቃ ሰው ይነሣል የመንግሥቱንም ክብር አይሰጡትም፤ በቀስታ መጥቶ መንግሥቱን በማታለል ይገዛል።
22፤ የሚጐርፍም ሠራዊት ከፊቱ ይወሰዳል፥ እርሱና የቃል ኪዳኑ አለቃ ይሰበራሉ።
23፤ ከእርሱም ጋር ከተወዳጀ በኋላ በተንኰል ያደርጋል፤ ከጥቂትም ሕዝብ ጋር ወጥቶ ይበረታል።
24፤ በቀስታ ከአገር ሁሉ ወደ ለመለመችው ክፍል ይገባል፤ አባቶቹና የአባቶቹ አባቶች ያላደረጉትንም ያደርጋል፤ ብዝበዛውንና ምርኮውንም ሀብቱንም በመካከላቸው ይበትናል፤ በምሽጎችም ላይ እስከ ጊዜው ድረስ አሳቡን ይፈጥራል።
25፤ በታላቅም ሠራዊት ሆኖ ኃይሉንና ልቡን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያስነሣል፤ የደቡብም ንጉሥ በታላቅና በብዙ ሠራዊት ሆኖ በሰልፍ ይዋጋል፤ ነገር ግን አሳብ በእርሱ ላይ ይፈጥራሉና አይጸናም።
26፤ መብሉንም የሚበሉ ሰዎች ይሰብሩታል፤ ሠራዊቱም ይጐርፋል፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ።
27፤ እነዚህም ሁለት ነገሥታት ክፋትን ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ያስባሉ፥ በአንድ ገበታም ተቀምጠው ሐሰት ይናገራሉ፤ ነገር ግን ፍጻሜው እስከ ተወሰነው ጊዜ ነውና አይከናወንላቸውም።
28፤ ከብዙም ሀብት ጋር ወደ ምድሩ ይመለሳል፥ ልቡም በተቀደሰ ቃል ኪዳን ላይ ይሆናል፤ ፈቃዱንም ያደርጋል፥ ወደ ገዛ ምድሩም ይመለሳል።
29፤ በተወሰነውም ጊዜ ይመለሳል ወደ ደቡብም ይመጣል፤ ነገር ግን ኋለኛው እንደ ፊተኛው አይሆንም።
30፤ የኪቲም መርከቦች ይመጡበታልና ስለዚህ አዝኖ ይመለሳል፥ በቅዱሱም ቃል ኪዳን ላይ ይቈጣል፥ ፈቃዱንም ያደርጋል፤ ተመልሶም ቅዱሱን ቃል ኪዳን የተዉትን ሰዎች ይመለከታል።
31፤ ከእርሱም ጋር ሠራዊቶች ይቆማሉ፥ መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ፥ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፥ የጥፋትንም ርኵሰት ያቆማሉ።
32፤ ቃል ኪዳኑን የሚበድሉትንም በማታለል ያስታል፤ ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ፥ ያደርጋሉም።
33፤ በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥበበኞች ብዙ ሰዎችን ያስተምራሉ፤ ነገር ግን በሰይፍና በእሳት ነበልባል በምርኮና በመበዝበዝ ብዙ ዘመን ይወድቃሉ።
34፤ በወደቁም ጊዜ በጥቂት እርዳታ ይረዳሉ፤ ብዙ ሰዎችም በግብዝነት ወደ እነርሱ ተባብረው ይሰበሰባሉ።
35፤ እስከ ተወሰነውም ዘመን ይሆናልና ከጥበበኞቹ አያሌዎቹ እስከ ፍጻሜ ዘመን ይነጥሩና ይጠሩ ይነጡም ዘንድ ይወድቃሉ።
36፤ ንጉሡም እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ ራሱንም ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ በአማልክት ሁሉ ላይ ራሱን ታላቅ ያደርጋል፥ በአማልክትም አምላክ ላይ በትዕቢት ይናገራል፤ ቍጣም እስኪፈጸም ድረስ ይከናወንለታል፥ የተወሰነው ይደረጋልና።
37፤ የአባቶቹንም አማልክት የሴቶችንም ምኞት አይመለከትም፤ ራሱንም በሁሉ ላይ ታላቅ ያደርጋልና አማልክትን ሁሉ አይመለከትም።
38፤ በእነዚህ ፋንታ ግን የአምባዎቹን አምላክ ያከብራል፤ አባቶቹም ያላወቁትን አምላክ በወርቅና በብር በዕንቍና በከበረ ነገር ያከብረዋል።
39፤ በእንግዳም አምላክ እርዳታ በጽኑ አምባ ላይ ያደርጋል፤ ለሚያውቁት ክብር ያበዛላቸዋል፥ በብዙም ላይ ያስገዛቸዋል፥ ምድርንም በዋጋ ይከፍላል።
40፤ በፍጻሜ ዘመንም የደቡብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል፤ የሰሜንም ንጉሥ ከሰረገሎችና ከፈረሰኞች ከብዙም መርከቦች ጋር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣበታል፤ ወደ አገሮችም ይገባል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል።
41፤ ወደ መልካሚቱም ምድር ይገባል፥ ብዙ አገሮችም ይወድቃሉ፤ ነገር ግን ኤዶምያስና ሞዓብ ከአሞንም ልጆች የበለጡት ከእጁ ይድናሉ።
42፤ እጁን በአገሮች ላይ ይዘረጋል፥ የግብጽም ምድር አታመልጥም።
43፤ በወርቅና በብርም መዝገብ ላይ፥ በከበረችም በግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሠለጥናል፤ የልብያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይከተሉታል።
44፤ ከምሥራቅና ከሰሜን ግን ወሬ ያውከዋል፤ ብዙ ሰዎችንም ይገድል ዘንድና ፈጽሞ ያጠፋ ዘንድ በታላቅ ቍጣ ይወጣል።
45፤ ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና በከበረው በቅዱስ ተራራ መካከል ይተክላል፤ ወደ ፍጻሜው ግን ይመጣል፥ ማንም አይረዳውም።