መጽሐፈ አስቴር። 8
1፤ በዚያም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የአይሁድን ጠላት የሐማን ቤት ለንግሥቲቱ ለአስቴር ሰጠ። አስቴርም ለእርስዋ ምን እንደ ሆነ ነግራው ነበርና መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ፊት ገባ።
2፤ ንጉሡም ከሐማ ያወለቀውን ቀለበቱን አወጣ፥ ለመርዶክዮስም ሰጠው። አስቴርም በሐማ ቤት ላይ መርዶክዮስን ሾመች።
3፤ አስቴርም እንደ ገና በንጉሡ ፊት ተናገረች፤ በእግሩም ላይ ወድቃ እያለቀሰች የአጋጋዊውን የሐማን ክፋትና በአይሁድ ላይ የተተነኰለውን ተንኰል ይሽር ዘንድ ለመነችው።
4፤ ንጉሡም የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፤ አስቴርም ተነሥታ በንጉሡ ፊት ቆመችና።
5፤ ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው፥ በፊቱም ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ ይህም ነገር በፊቱ ቅን ቢሆን፥ እኔም በእርሱ ዘንድ ተወድጄ እንደ ሆነ፥ አጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አገር ሁሉ ያሉትን አይሁድ ለማጥፋት የጻፈው ተንኰል ይገለበጥ ዘንድ ይጻፍ።
6፤ እኔ በሕዝቤ ላይ የሚወርደውን ክፉ ነገር አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ወይስ የዘመዶቼን ጥፋት አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? አለች።
7፤ ንጉሡም አርጤክስስ ንግሥቲቱን አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን። እነሆ የሐማን ቤት ለአስቴር ሰጥቻለሁ፥ እርሱም እጆቹን በአይሁድ ላይ ስለ ዘረጋ በግንድ ላይ ተሰቀለ።
8፤ በንጉሡ ስም የተጻፈና በንጉሡ ቀለበት የታተመ አይገለበጥምና እናንተ ደግሞ ደስ የሚያሰኛችሁን በንጉሡ ስም ስለ አይሁድ ጻፉ፥ በንጉሡም ቀለበት አትሙ አላቸው።
9፤ በዚያን ጊዜም ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሀያ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፤ መርዶክዮስም ስለ አይሁድ እንዳዘዘው ሁሉ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ላሉ ሹማምትና አለቆች አዛውንትም ለእያንዳንዱም አገር እንደ ጽሕፈቱ ለእያንዳንዱም ሕዝብ እንደ ቋንቋው ለአይሁድም እንደ ጽሕፈታቸውና እንደ ቋንቋቸው ተጻፈ።
10፤ በንጉሡም በአርጤክስስ ስም አስጻፈው፥ በንጉሡም ቀለበት አሳተመው፤ ደብዳቤውንም በንጉሡ ፈረስ ቤት በተወለዱት፥ ለንጉሡም አገልግሎት በተለዩ በፈጣን ፈረሶች በተቀመጡ መልእክተኞች እጅ ሰደደው።
11፤ በዚያም ደብዳቤ በከተሞቹ ሁሉ የሚኖሩት አይሁድ እንዲሰበሰቡ፥ ለሕይወታቸውም እንዲቆሙ፥ በጥል የሚነሡባቸውን የሕዝቡንና የአገሩን ሠራዊት ሁሉ ከሕፃናቶቻቸውና ከሴቶቻቸው ጋር እንዲያጠፉና እንዲገድሉ እንዲደመስሱም፥ ምርኮአቸውንም እንዲዘርፉ ንጉሡ ፈቀደላቸው።
12፤ ይህም አዳር በሚባለው በአሥራ ሁለተኛው ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን በንጉሡ በአርጤክስስ አገሮች ሁሉ በአንድ ቀን እንዲሆን ነው።
13፤ አይሁድም ጠላቶቻቸውን እንዲበቀሉ በዚያ ቀን ይዘጋጁ ዘንድ የደብዳቤው ቅጅ በየአገሩ ላሉ አሕዛብ ሁሉ ታወጀ።
14፤ ለንጉሡ አገልግሎት በተለዩ በፈጣን ፈረሶች የተቀመጡት መልእክተኞች በንጉሡ ትእዛዝ ተርበትብተውና ቸኵለው ወጡ፤ አዋጁም በሱሳ ግንብ ተነገረ።
15፤ መርዶክዮስም በሰማያዊና በነጭ ሐር የተሠራውን የንጉሡን የክብር ልብስ ለብሶ ታላቅም የወርቅ አክሊል ደፍቶ ከጥሩ በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ የተሠራ መጐናጸፊያ ተጐናጽፎ ከንጉሡ ፊት ወጣ፤ የሱሳም ከተማ ደስ አላት፥ እልልም አለች።
16፤ ለአይሁድም ብርሃንና ደስታ ተድላና ክብርም ሆነ።
17፤ የንጉሡም ትእዛዝና አዋጅ በደረሰበት አገርና ከተማ ሁሉ ለአይሁድ ደስታና ተድላ፥ የግብዣም ቀን መልካምም ቀን ሆነ። አይሁድንም መፍራት ስለ ወደቀባቸው ከምድር አሕዛብ ብዙ ሰዎች አይሁድ ሆኑ።