መጽሐፈ ነህምያ። 3
1፤ ታላቁም ካህን ኤልያሴብ ወንድሞቹም ካህናት ተነሥተው የበግ በር ሠሩ፤ ቀደሱትም፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ እስከ ሃሜአ ግንብና እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት።
2፤ በአጠገቡ የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገባቸውም የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ።
3፤ የሃስናአ ልጆችም የዓሣ በር ሠሩ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ።
4፤ በአጠገባቸውም የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት አደሰ። በአጠገባቸውም የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም አደሰ። በአጠገባቸውም የበዓና ልጅ ሳዶቅ አደሰ።
5፤ በአጠገባቸውም ቴቁሐውያን አደሱ፤ ታላላቆቻቸው ግን ለጌታቸው ሥራ አንገታቸውን አላዋረዱም።
6፤ የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም አሮጌውን በር አደሱ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ።
7፤ በአጠገባቸውም ገባዖናዊው መልጥያና ሜሮኖታዊው ያዶን፥ የወንዙም ማዶ አለቃ ግዛት የሆኑ የገባዖንና የምጽጳ ሰዎች አደሱ።
8፤ በአጠገባቸውም ወርቅ አንጥረኛው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል አደሰ። በአጠገቡም ከሽቱ ቀማሚዎች የነበረ ሐናንያ አደሰ፤ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ ኢየሩሳሌምን ጠገኑ።
9፤ በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታ አለቃ የሆር ልጅ ረፋያ አደሰ።
10፤ በአጠገባቸውም የኤርማፍ ልጅ ይዳያ በቤቱ አንጻር ያለውን አደሰ። በአጠገቡም የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ አደሰ።
11፤ የካሪም ልጅ መልክያ፥ የፈሐት ሞዓብ ልጅም አሱብ ሌላውን ክፍልና የእቶኑን ግንብ አደሱ።
12፤ በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታና የመንደሮችዋ አለቃ የአሎኤስ ልጅ ሰሎም አደሰ።
13፤ ሐኖንና የዛኖዋ ሰዎችም የሸለቆውን በር አደሱ፤ ሠሩት፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ፤ ደግሞም እስከ ጕድፍ መጣያው በር ድረስ አንድ ሺህ ክንድ የሚሆን ቅጥር ሠሩ።
14፤ የቤትሐካሪምም ግዛት አለቃ የሬካብ ልጅ መልክያ የጕድፍ መጣያውን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ።
15፤ የምጽጳም ግዛት አለቃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም የምንጩን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ከደነውም፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ፤ ከዳዊትም ከተማ እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ያለውን የሼላን መዋኛ ቅጥር ሠራ።
16፤ ከእርሱም በኋላ የቤትጹር ግዛት እኵሌታ አለቃ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ በዳዊት መቃብር አንጻር እስካለው ስፍራ፥ እስከ ተሠራውም መዋኛ፥ እስከ ኃያላኑም ቤት ድረስ አደሰ።
17፤ ከእርሱም በኋላ ሌዋውያንና የባኒ ልጅ ሬሁም አደሱ። በአጠገባቸውም የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ ሐሸብያ ስለ ግዛቱ አደሰ።
18፤ ከእርሱም በኋላ የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይ ወንድሞቹም አደሱ።
19፤ በአጠገቡም የምጽጳ አለቃ የኢያሱ ልጅ ኤጽር በማዕዘኑ አጠገብ በጦር መሣሪያ ቤት አንጻር ሌላውን ክፍል አደሰ።
20፤ ከእርሱም በኋላ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማዕዘኑ ጀምሮ እስከ ታላቁ ካህን እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ድረስ ሌላውን ክፍል ተግቶ አደሰ።
21፤ ከእርሱም በኋላ የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ ኤልያሴብ ቤት መጨረሻ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ።
22፤ ከእርሱም በኋላ የቈላው ሰዎች ካህናቱ አደሱ።
23፤ ከእነርሱም በኋላ ብንያምና አሱብ በቤታቸው አንጻር ያለውን አደሱ። ከእነርሱም በኋላ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን አደሰ።
24፤ ከእርሱም በኋላ የኤንሐደድ ልጅ ቢንዊ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ።
25፤ የኡዛይ ልጅ ፋላል በማዕዘኑ አንጻር ያለውንና በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ከላይኛው የንጉሡ ቤት ወጥቶ የቆመውን ግንብ ሠራ። ከእርሱም በኋላ የፋሮስ ልጅ ፈዳያ ሠራ።
26፤ ናታኒምም በዖፌል በውኃው በር አንጻር በምሥራቅ በኩል ወጥቶ በቆመው ግንብ አጠገብ እስካለው ስፍራ ድረስ ተቀመጡ።
27፤ ከእርሱም በኋላ ቴቁሐውያን ወጥቶ በቆመው በታላቁ ግንብ አንጻር ያለውን እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ሌላውን ክፍል አደሱ።
28፤ ከፈረሱ በር በላይ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየቤታቸው አንጻር አደሱ።
29፤ ከዚያ በኋላ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ አንጻር አደሰ። ከእርሱም በኋላ የምሥራቁን በር ጠባቂ የሴኬንያ ልጅ ሸማያ አደሰ።
30፤ ከእርሱ በኋላ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛው ልጁ ሐኖን ሌላውን ክፍል አደሱ። ከዚያም በኋላ የበራክያ ልጅ ሜሱላም በጓዳው አንጻር ያለውን አደሰ።
31፤ ከእርሱም በኋላ ከወርቅ አንጥረኞቹ የነበረ መልክያ እስከ ናታኒምና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት ድረስ በሐሚፍቃድ በር አንጻር ያለውን እስከ ማዕዘኑ መውጫ ድረስ አደሰ።
32፤ ከማዕዘኑም መውጫ ጀምረው እስከ በጉ በር ድረስ ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች አደሱ።