መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ። 2
1፤ ዳዊትም የሚሞትበት ቀን ቀረበ፤ ልጁንም ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው።
2፤ እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤
3፤ በርታ ሰውም ሁን፤ የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ።
4፤ ይኸውም ደግሞ እግዚአብሔር ስለ እኔ። ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በእውነት ቢሄዱ ከእስራኤል ዙፋን ሰው አይቈረጥብህም ብሎ የተናገረውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው።
5፤ አንተም ደግሞ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ፥ ሁለቱን የእስራኤልን ጭፍራ አለቆች የኔር ልጅ አበኔርን የዬቴሩንም ልጅ አሜሳይን ገድሎ፥ በእኔ ላይ ያደረገውን ታውቃለህ፤ የሰልፉንም ደም በሰላም አፈሰሰ፥ በወገቡም ባለው ድግና በእግሩ ባለው ጫማ ንጹሕ ደም አኖረ።
6፤ አንተም እንደ ጥበብህ አድርግ፥ ሽበቱንም በሰላም ወደ መቃብር አታውርደው።
7፤ ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ ቀርበውኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች መልካም ቸርነት አድርግላቸው፥ በማዕድህም ከሚበሉት መካከል ይሁኑ።
8፤ እኔም ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ ብርቱ እርግማን የረገመኝ የብራቂም አገር ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ፥ እነሆ፥ በአንተ ዘንድ ነው፤ እርሱ ግን ዮርዳኖስን በተሻገርሁ ጊዜ ሊቀበለኝ ወረደ፥ እኔም። በሰይፍ አልገድልህም ብዬ በእግዚአብሔር ምዬለታለሁ።
9፤ አንተ ግን ጥበበኛ ሰው ነህና ያለ ቅጣት አትተወው፤ የምታደርግበትንም አንተ ታውቃለህ፥ ሽበቱንም ከደም ጋር ወደ መቃብር አውርድ።
10፤ ዳዊትም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ።
11፤ ዳዊትም በእስራኤል ላይ የነገሠው ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። በኬብሮን ሰባት ዓመት ነገሠ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።
12፤ ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ ጸና።
13፤ የአጊት ልጅ አዶንያስም ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ፤ እርስዋም። ወደ እኔ መምጣትህ በሰላም ነውን? አለች፤
14፤ እርሱም። በሰላም ነው አለ። ደግሞም። ከአንቺ ጋር ጉዳይ አለኝ አለ፤ እርስዋም። ተናገር አለች።
15፤ እርሱም። መንግሥቱ ለእኔ እንደ ነበረ፥ እስራኤልም ሁሉ ንጉሥ እሆን ዘንድ ፊታቸውን ወደ እኔ አድርገው እንደ ነበረ አንቺ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖለታልና መንግሥቱ ከእኔ አልፎ ለወንድሜ ሆኖአል።
16፤ አሁንም አንዲት ልመና እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ አለ። እርስዋም። ተናገር አለችው።
17፤ እርሱም። አያሳፍርሽምና ሱነማይቱን አቢሳን ይድርልኝ ዘንድ ለንጉሡ ለሰሎሞን እንድትነግሪው እለምንሻለሁ አለ።
18፤ ቤርሳቤህም። መልካም ነው፥ ስለ አንተ ለንጉሡ እነግረዋለሁ አለች።
19፤ ቤርሳቤህም የአዶንያስን ነገር ትነግረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ገባች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ ሳማትም፥ በዙፋኑም ተቀመጠ፤ ለንጉሡም እናት ወንበር አስመጣላት፥ በቀኙም ተቀመጠች።
20፤ እርስዋም። አንዲት ታናሽ ልመና እለምንሃለሁ፤ አታሳፍረኝ አለች። ንጉሡም። እናቴ ሆይ፥ አላሳፍርሽምና ለምኝ አላት።
21፤ እርስዋም። ሱነማይቱ አቢሳ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት አለች።
22፤ ንጉሡም ሰሎሞን ለእናቱ መልሶ። ሱነማይቱን አቢሳን ለአዶንያስ ለምን ትለምኝለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ነውና መንግሥትን ደግሞ ለምኚለት፤ ካህኑም አብያታርና የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ደግሞ ከእርሱ ጋር ናቸው አላት።
23፤ ንጉሡም ሰሎሞን። አዶንያስ ይህን ቃል በሕይወቱ ላይ አለመናገሩ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ።
24፤ አሁንም ያጸናኝ፥ በአባቴም በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠኝ፥ እንደ ተናገረውም ቤትን የሠራልኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ዛሬ አዶንያስ ፈጽሞ ይገደላል ብሎ በእግዚአብሔር ማለ።
25፤ ንጉሡም ሰሎሞን የዮዳሄን ልጅ በናያስን ላከ፤ እርሱም ወደቀበት፥ ሞተም።
26፤ ንጉሡም ካህኑን አብያታርን። አንተ ዛሬ የሞት ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፥ አባቴም የተቀበለውን መከራ ሁሉ አንተ ስለ ተቀበልህ አልገድልህምና በዓናቶት ወዳለው ወደ እርሻህ ሂድ አለው።
27፤ በሴሎም በዔሊ ቤት ላይ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አወጣው።
28፤ ለኢዮአብም ወሬ ደረሰለት፤ ኢዮአብም አቤሴሎምን አልተከተለም ነበር እንጂ አዶንያስን ተከትሎ ነበር። ኢዮአብም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ።
29፤ ንጉሡም ሰሎሞን ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሠዊያውን እንደ ያዘ ሰማ፤ ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በናያስን፥ ሂድ ውደቅበት ብሎ አዘዘው።
30፤ በናያስም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን መጥቶ። ንጉሡ። ውጣ ይልሃል አለው፤ እርሱም። በዚህ እሞታለሁ እንጂ አልወጣም አለ። በናያስም። ኢዮአብ የተናገረው ቃል የመለሰልኝም እንዲህ ነው ብሎ ወደ ንጉሡ ወሬ አመጣ።
31፤ ንጉሡም አለው። እንደ ነገረህ አድርግ፤ ኢዮአብም በከንቱ ያፈሰሰውን ደም ከእኔና ከአባቴ ቤት ታርቅ ዘንድ ገድለህ ቅበረው።
32፤ አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእርሱ የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎች፥ የእስራኤልን ሠራዊት አለቃ የኔርን ልጅ አበኔርን፥ የይሁዳንም ሠራዊት አለቃ የዬቴርን ልጅ አሜሳይን፥ በሰይፍ ገድሎአልና እግዚአብሔር ደሙን በራሱ ላይ ይመልሰው።
33፤ ደማቸውም በኢዮአብ ራስና በዘሩ ራስ ላይ ለዘላለም ይመለስ፤ ለዳዊት ግን ለዘሩና ለቤቱ ለዙፋኑም የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ይሁን።
34፤ የዮዳሄም ልጅ በናያስ ወጥቶ ወደቀበት ገደለውም፤ በምድረ በዳም ባለው በቤቱ ተቀበረ።
35፤ ንጉሡም በእርሱ ፋንታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን የሠራዊቱ አለቃ አደረገ፤ በአብያታርም ፋንታ ካህኑን ሳዶቅን አደረገ።
36፤ ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራውና። በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፥ ወዲህና ወዲያም አትውጣ።
37፤ በወጣህበትም ቀን፥ የቄድሮንንም ፈፋ በተሻገርህበት ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ፤ ደምህ በራስህ ላይ ይሆናል አለው።
38፤ ሳሚም ንጉሡን። ነገሩ መልካም ነው፤ ጌታዬ ንጉሥ እንደ ተናገረ ባሪያህ እንዲሁ ያደርጋል አለው፤ ሳሚም በኢየሩሳሌም ብዙ ቀን ተቀመጠ።
39፤ ከሦስት ዓመትም በኋላ ከሳሚ ባሪያዎች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ሳሚንም። እነሆ፥ ባሪያዎችህ በጌት ናቸው ብለው ነገሩት።
40፤ ሳሚም ተነሣ፥ አህያውንም ጭኖ ባሪያዎቹን ይሻ ዘንድ ወደ ጌት ወደ አንኩስ ዘንድ ሄደ፤ ሳሚም ሄዶ ባሪያዎቹን ከጌት አመጣ።
41፤ ሰሎሞንም ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ እንደ ተመለሰ ሰማ።
42፤ ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራና። ወዲህና ወዲያ ለመሄድ በወጣህ ቀን ፈጽመህ እንድትሞት እወቅ ብዬ በእግዚአብሔር አላስማልሁህምን? ወይስ አላስመሰከርሁብህምን? አንተም። ቃሉ መልካም ነው፥ ሰምቻለሁ አልኸኝ።
43፤ የእግዚአብሔርን መሐላ እኔስ ያዘዝሁህን ትእዛዝ ስለ ምን አልጠበቅህም? አለው።
44፤ ንጉሡም ደግሞ ሳሚን። አንተ በአባቴ በዳዊት ላይ የሠራኸውን ልብህም ያሰበውን ክፋት ሁሉ ታውቃለህ፤ እግዚአብሔርም ክፋትህን በራስህ ላይ ይመልሳል።
45፤ ንጉሡ ሰሎሞን ግን የተባረከ ይሆናል፥ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ይጸናል አለው።
46፤ ንጉሡም የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፥ ወጥቶም ወደቀበት፥ ሞተም። መንግሥትም በሰሎሞን እጅ ጸና። a